ምርትን በብቸኝነት ማስመጣት ወይም ማከፋፈልን የሚከለክለው ህግ ዛሬም አልተከበረም

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 29 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የንግድ ውድድር እንዲኖርና ምርት በተወሰኑ ሰዎች እጅ ገብቶ ዋጋን መቆጣጠር በግለሰቦች እጅ እንዳይገባ ብቸኛ አስመጪነት ወይም አከፋፋይነት መከልከሉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ከውጭ በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶች ላይ ውድድር እንዲኖር ምርት በጥቂት ግለሰቦች እጅ እንዳይከማች፥ የሸቀጦች ዋጋ በግለሰቦች ሳይሆን በገበያ እንዲሆን በ2008 ዓ.ም ህግ ወጥቶ ነበር።

በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ውስጥ በአንቀጽ 38 ውስጥ ብቸኛ አስመጪ ወይም አከፋፋይ ሆኖ መስራት የተከለከለ ሲሆን፥ ከስራው ባህሪና ሃገራዊ ጥቅም አንጻር፤ ብቸኛ አስመጭ ወይም አከፋፋይ ሆኖ መስራት የሚቻልባቸው የንግድ ስራ መስኮችን በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ሊያወጣ እንደሚችል ተጠቅሷል።

ሆኖም አስመጪና አከፋፋይ ሳይኖር የፍጆታ እቃዎችን ጭምር በብቸኝነት የማስመጣቱና ማከፋፈሉ ስራ የቀጠለ ነው የሚመስለው።

አስመጪዎችም ምርቶችን ከተለያዩ ሃገራት አምራቾች ገዝተው ሀገር ውስጥ ለማከፋፈል ቢጠይቁም፥ አምራቾቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርቶቻቸውን የሚሰጡት አስመጪና አከፋፋይ እንዳለ በመጥቀስ ጥያቄያቸውን እንደማይቀበሏቸው ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የፍጆታ እቃዎች ንግድ ስራ ዘርፍ ወይም አለ በጅምላ ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ አዳነ አለሙ፥ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ውስጥ ብቸኛ አስመጪነት ከተከለከለ በኋላ ይህ እንዳጋጠማቸው ይጠቅሳሉ።

የአሜሪካው ፕሮክተር ኤንድ ጃምብል ኩባንያ፣ መሰረቱን ስዊዘርላንድ ያደረገው ኔስትል ኩባንያ እና የዱባዩ ኦምኒኮም ኩባንያ ምርቶቻችንን ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ አስመጪና አከፋፋይ ነው የምንሰጠው የሚል ምላሽ እንደሰጡም ነው የሚጠቅሱት።

ብቸኛ አስመጪና ላኪነት በህግ ከተከለከለ በኋላም ቢሆን ግን አሁንም በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የፍጆታ እቃዎችን ሳይቀር ብቸኛ አስመጪና አከፋፋይ ነን ብለው የሚያስተዋውቁ ኩባንያዎች አሉ።

አቶ አዳነ እንደሚሉትም አሁን ባለው ሁኔታ ብቸኛ አስመጪና አከፋፋይ የሚኖር ከሆነ ዋጋን ማረጋጋት አይቻልም፤ አስመጪዎቹ ምርቶቹን በፈለጉት ዋጋ እንደሚሸጡ በመጥቀስ።

የአስመጪዎች ቅሬታ እንዳለ ሆኖ በአደባባይ ብቸኛ አስመጪና አከፋፋይ ነን የሚሉ ኩባንያዎች እያደረጉት ስላለው ነገር አልተጠየቁም።

በንግድ ሚኒስቴር የሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አማካሪ አቶ ደሬሳ ቆቱም፥ ህጉ በይፋ ወደ ተግባር የገባ ቢሆንም በዚህ ተግባር ላይ አለን እያሉ የሚያስተዋውቁትን ከመቅጣት አንጻር አለመሰራቱን ይገልጻሉ።

በዘርፉ ላይ ያሉ ግለሰቦች ደግሞ አንዳንድ ምርቶች ለጥራታቸውና ለህብረተሰቡ ደህንነት ሲባል፥ አቅማቸው ከፍ ባሉ ብቸኛ አስመጪዎች እንዲመጡ ሊደረግ እንደሚችል ያነሳሉ።

በሀገር ውስጥ የወጣው አዋጅ ግን ይህን ወደ ታች አውርዶ ከመተንተን አንጻር ክፍተት ታይቶበታል።

ብቸኛ አስመጪነትና አከፋፋይነት ይቅር ሲባል ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ብዛት በመንግስት ተጠንቶና ለውጭ ሃገር አምራቾች፥ ምርቶቹ በአንድ አስመጪ ብቻ እንደማይመጡ ማስረዳትና የውድድሩን ጠቃሚነት ማሳየትንም ይጠይቃል።

ሆኖም እነዚህ ስራዎች አልተሰሩም፤ በዚህ ላይ ያለን ሰው የመቅጫ መንገዱም በተገቢው መንገድ ግልጽ አይደለም።

የገበያ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ አላዛር አህመድ በበኩላቸው፥ ብቸኛ አስመጪና አከፋፋዮች በሚሰሩበት ክፍተት እንኳ የትርፍ ህዳግ ሊቀመጥላቸው ሲገባ ይህ አለመሆኑን ነው የሚናገሩት።

በንግድ ሚኒስቴር የሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አማካሪው አቶ ደሬሳ ህጉን ከመተግበር አንጻር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደፊት የሚሰራበት ነው ብለዋል።
ቢሰራበት ኑሮን ሊያቀል የሚችለው ህግ ግን አሁን ላይ አስታዋሽ ይፈልጋል።

 

በካሳዬ ወልዴ