ውሺ ቁጥር 1 የተባለው የቻይና ኩባንያ በድሬ ዳዋ የተቀናጀ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሊያቋቁም ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ውሺ ቁጥር 1 የተባለ የቻይና ኩባንያ በድሬ ዳዋ ከተማ የተቀናጀ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራረመ።

ውሺ ቁጥር 1 የተባለው ኩባንያ የጉዎሉያን ዴቨሎፕመንት ግሩፕ አካል ሲሆን፥ መቀመጫውን የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ውሺ ከተማ ያደረገ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያ ነው።

ኩባንያው በድሬዲዋ ከተማ አስተዳደር የተቀናጀ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የኢንቨስትመንት ስምምነት ሰነድ መፈረሙን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ድርጅቱ ከ100 ዓመት በላይ ባካበተው ምርጥና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ የገበያ ትስስር እንዱሁም የዳበረ የማምረት ልምድ ሀገሪቱን በዘርፉ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ስምምነቱም የውሺ ከተማ ከንቲባና በሻንግሃይ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል አምባሳደር ሙላ ታረቀኝ በተገኙበት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በድርጅቱ ሃሊፊዎች መካከል ጥቅምት 23 2010 ዓ.ም በውሺ ከተማ ተፈርሟል።

WUSHI.jpg

በስምምነቱም መሰረት ድርጅቱ የሚያቋቁመው ፋብሪካ ክርና ጨርቃ ጨርቅ የሚያመርት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ፥ ኢንቨስትመንቱ መንግስት ሀገሪቱን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንደስትሪ ማዕከል እንድትሆን ብሎም በአፍሪካ ቀዲሚ የማምረቻ ኢንደስትሪ መዳረሻ ለማድረግ እያከናወነ ላለው እንቅስቃሴ ተጨማሪ እቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የውሺ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው፥ የከተማው አስተዳደር የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ኢንቨስትመንት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት ድርጅቱ በዓመት ከ26 ሺህ ቶን በላይ ክር እና ከ30 ሚሊየን ሜትር በላይ ጨርቅ በማምረት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።

75 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ኮርያ እና በተቀሩት የደቡብ ምስራቅ እሲያ ሀገራት በመላክ ለስመጥርና ዓለም አቀፍ ብራንዶች ያቀርባል።