ሀገሪቱን ከማዕድን ተጠቃሚ የሚያደርግና የዘርፉን ችግሮች የሚፈታ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገሪቱን ከማዕድን ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርግና የዘርፉን ችግሮች የሚፈታ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ረቂቅ ፖሊሲውንና የዘርፉን የስራ እቅስቃሴ በአዳማ ከተማ ገምግሟል።

የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ፥ የዘርፉን ችግሮች በመፍታትና መፍትሄ በመስጠት ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የዘርፉ ተዋናዮች በትብብር መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

በተለይ በወርቅ ላይ ከባንክ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች እንደሚፈቱና የባንክ የእፎይታ ጊዜው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚፈቀድም ጠቁመዋል።

የወርቅ የቅበላ መጠኑ ከነበረበት ከ150 ግራም ወደ 50 ግራም ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት።

አቶ ሞቱማ ወርቅ በሚመረትባቸው ወረዳዎች አካባቢ የባንክ ተደራሽነትን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ በህግ ማዕቀፍ እንዲመራ የተደረገ ሲሆን፥ በተለያዩ ጊዜያት በነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ ምክንያት የማዕድን ስራዎችን የማስተዳደር ስራ በተለያየ መንገድ ሲመራ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንግስት የማዕድኑን ዘርፍ፥ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በመረዳት የማዕድን አዋጅ አውጥቶ እየሰራ ሲሆን፥ ረቂቅ የማዕድን ፖሊሲ መዘጋጀቱም ተነግሯል።

ረቂቅ ፖሊሲው የሀገሪቱን ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት በማጠናከር፣ ለዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እንደሚያሳድግ ነው የተመላከተው።

ጠንካራ እና ትርፋማ የግል ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚፈጥር ሰፊ መሰረት ያለው የማዕድን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሰረት ለማድረግ የሚያስችል ነውም ተብሏል።

ረቂቅ የማዕድን ፖሊሲው ከክልሎች ጋር የተገመገመ ሲሆን፥ በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እስከታች ድረስ ወርዶ አስተያየት እንደሚሰጥበት ነው የተጠቆመው።

ፖሊሲው ፀድቆ ሲወጣ የዘርፉን ችግሮች የሚፈታና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ከማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።