የሀር ምርትን በሀገር ውስጥ ከማምረት አንጻር ክፍተት መኖሩ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሀገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የሀር ምርትን በሀገር ውስጥ ከማምረት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት አለ ተባለ።

ለሀር ምርት ተሰማሚ የሆኑ አራት ክልሎች መኖራቸው ቢረጋገጥም ምርቱ በስፋት እንዳልተሰራበትም ነው የተነገረው።

ከጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት ብቻ 100 ቶን የሀር ምረት ቢያስፈልግም፤ በሀገር ውስጥ ተመርቶ የቀረበው ግን 5 ቶን ብቻ ነው።

በእንስሳት እና አሳ ሀብት ሚኒስቴር የማር እና የሀር ሀብት ልማት ተወካይ ዳሬክተር አቶ ደምሰው ዋቅጅራ፥ የሀር ልማት አሰራሩ ቀላልና ማንኛውም ሰው ሊሳተፍበት የሚችል ቢሆንም፤ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለውን እንኳ ማመቅረብ አልተቻለም ይላሉ።

አሁን ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀርን በስፋት ለማምረት ከግብርና ምርም ማእከላት እና እና ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀር ትል ቴክኖሎጂን ከውጭ በማምጣት እና ጥናት እና ምርምር በማድረግ እየሰራ የሚገኘው የመልካሳ ምርምር ማእከል አንዱ ሲሆን፥ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች ለሀር ምርት እርባታ ምቹ መሆናቸውን አስታውቋል።

በማእከሉ የሀር ተመራማሪ እና የእንስሳት ስራ ሂደት ተጠሪ አቶ አብይ ጥላሁን፥ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሆነ አማራጭ የገበያ ምንጭ ለመሆን የሚችል አቅም መኖሩን አንስተዋል።

በትልቅ ካፒታል በኢንቨስትመንትም ሆነ በአነስተኛ አርሶ አደር ደረጃ ሊሰራ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ደምሰው ዋቅጅራ በበኩላቸው፥ አሁን ያለውን ጅምር ስራዎች በማጠናከር ረገድ ኤ.ሲ.ፒ.ኤ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በደቡብ ክልል 2 ሺህ 500 ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በ2009 ዓ.ም 5 ነጥብ 8 ቶን ምርት የተገኘ ሲሆን፥ በተያዘው በጀተ ዓመት በእጥፍ በማሳደግ 10 ቶን ለማምረት እቅድ ተይዟል።

ይህ አሀዝ በየዓመቱ በእጥፍ እንዲያድግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የተገለጸው፡፡

 

 

 

 

 

በሰርካለም ጌታቸው