በሙዳይ የባንክ ቁጠባ ተጠቀሚዎች ከ481 ሚሊየን ብር በላይ ተቆጥቧል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሙዳይ ባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ78 ሺ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰታወቀ።

በእነዚህ ተጠቃሚዎችም ከ481 ሚሊየን ብር በላይ መቆጠቡን ነው ባንኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያሳወቀው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሶስት ዓመት በፊት የጀመረው የሙዳይ ባንክ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በየቀኑ የሚያገኙትን ገቢ በቁጠባ መልክ እንዲያስቀምጡ የሚያስችል አገልግሎት ነው።

አገልግሎቱንም ባንኩ ባዘጋጀው ሙዳይ ውስጥ ተጠቃሚዎቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ከሳንቲም ጀምሮ የሚያስቀምጡበት ሲሆን፥ የሙዳዩ ቁልፍ በባንኩ ይቀመጣል።

ሙዳዩንም በወር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በመክፈት የተጠራቀመውን ገንዘብ ወደ ተጠቃሚዎቹ የባንክ ሂሳብ የሚያስቀምጥበት አሰራር ነው።

የባንኩ የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ፥ ይህን የቁጠባ ባህል ለማስፋት ባንኩ በዘመቻ መልክ በስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመትም በስፋት በሙዳይ የባንክ ቁጠባ ላይ ለመስራት መታቀዱን ነው አቶ በልሁ የሚያነሱት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ይህን እና መሰል የቁጠባ አማራጮችን በመተግበር ያለውን ተቀማጭ ገንዘብ እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።


በዙፋን ካሳሁን