በደቡብ ክልል የተደራጁ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረጉ አለመሆኑን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል የተደራጁ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ አለመሆኑን በተለይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በበኩሉም መዘግየቶች ቢኖሩም የተደራጁ ወጣቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል ለማመቻቸት እየሰራሁ ነው ብሏል።

በቢሮው የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ይዘዲን ሙስባህ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባዘጋጀው በቀጥታ የሬዲዮ ውይይት ላይ በከተማ 255 ሺህ በገጠር ደግሞ ከ300 ሺህ በላይ ወጣቶች በክልሉ ስራ ፈላጊ ሆነው መለየታቸውን ተናግረዋል።
የተደራጁ ወጣቶች በበኩላቸው ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ እንዳልሆነ እና ሙሰኝነት እና የጥቅም ትስስር እንደሚስተዋል ለጣቢያችን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ወጣቶቹ ለተደራጁ ማህበራት የሚደረገው ድጋፍና ክትትልም አነስተኛ መሆኑን ነው የገለፁት።

አቶ ይዘዲን ደግሞ በፌደራል ደረጃ ከተመደበው 10 ቢሊየን ብር ለደቡብ ክልል 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የተመደበ ሲሆን፥ እስካሁን 50 በመቶው ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረው፥ መዘግየቶች ቢኖሩም ወጣቶች ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም ይላሉ።

ለዚህም ከፌደራል መንግስት ተዘዋዋሪ ፈንድ ለክልሉ ከተሰጠው ውስጥ ቀሪውን 50 በመቶ ጨምሮ የክልሉ መንግስት የመደበው 200 ሚሊየን ብር ዞኖች እና ወረዳዎች የመደቡት ከ250 ሚሊየን ብር በላይ መኖሩን ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት ከተሰራጨው ገንዘብ የሚመለስ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ በየአካባቢው በመኖሩ የተደራጁ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት አመቺ መሆኑን አንስተዋል።

ማህበራቱ ስራውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆናቸውን የመከታተል እና መቆጣጠር እንዲሁም የድጋፍ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው ስራ አስኪያጁ የገለፁት።

የተደራጁ ማህበራትን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ጉቦ የሚጠይቁ እና የጥቅም ትስስር የሚፈጥሩ ሰራተኞች አሉ የሚለውን ወቀሳ ያመኑት አቶ ይዘዲን፥ ከወጣቶች ጋር በመወያየት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ችግሮችን በማስተካከል እና በማረጋገጥ እርምጃው እንደሚቀጥል አንስተው፥ ወጣቱም ስህተቶችን በመቆጣጠር ረገድ በባለቤትነት ስሜት አብሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።


በታደሰ ሽፈራው