ብሄራዊ ባንክ በ2 ዓመት የዘገየውን የ2ኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ ዘንድሮ አስጀምራለሁ አለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሁለት ዓመት በፊት ይጀመራል ተብሎ የዘገየውን የሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ በዚህ ዓመት እንደሚያስጀምር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ ይህንን ገበያ ባልኩት ጊዜ ማቋቋም ያልቻልኩት ስራውን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ጥናቶች በሚፈለገው ጊዜ ባለማለቃቸው ነው ብሏል ።

ጉዳዩን በባለቤትነት የያዘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በ2009 ዓ.ም ሀምሌ ወር ላይ የሁለተኛ ደረጃ ገበያውን ለማስጀመር እቅድ ይዞ ነበር።

የባንኩ ምክትል ገዢና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው፥ በወቅቱ አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው በተያዘለት ጊዜ መጀምር እንዳልተቻለ ይናገራሉ።

ገበያው ለኢትዮጵያ አዲስ ይዘት ያለው በመሆኑ ከዚሁ ጋር የሚገናኙ የህግ እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ከታሰበው በላይ ጊዜ መስወዱንም ገልፀዋል።

አሁን ላይ ግን የሚፈለጉ ቅድመ ሁኔታዎች በመጠናቀቃቸው በዚህ ዓመት ገበያው ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግን ገበያውን ለማስጀመር የሚያግዙ አሰራሮች መጠናቀቃቸውንም ዶክተር ዮሀንስ አስታውቀዋል።

የሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ ማለት በብዙ ሀገራት ተግባራዊ የሆነና ራሱን የቻለ ከፍተኛ የፋይናንስ ገበያ ማንቀሳቀሻ ነው።

ይህ ገበያ የሚያስፈልገው ከመጀመርያ ደረጃ የቦንድ ገበያ በኋላ ሰነዱን ለመለዋወጥ ነው።

ሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ በኢትዮጵያ መጀመር ማለት በዚያው ልክ በሀገሪቱ አዲስ የመገበያያ ስልት መጣ ማለት ሲሆን፥ ይህም በሰነድ መገበያየት ነው።

አንድ ግለሰብ ወይም ኩባንያ ከመንግስት ወይንም ከሌላ አካል ለመጀመርያ ገበያ በተወሰነ የጊዜ ገደብ የገዛውን ቦንድ የቦንዱ ማለቂያን ጊዜ ሳይጠብቅ በሚፈልገው ወቅት መጠቀም ያስችለዋል።

የሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ ሲተገበር ኩባንያዎች የገዟቸውን ሰነዶች ለመንግስት መመለስ ሳይጠበቅባቸው ለሌሎች ኩባንያዎች ሰነዶችን በመሸጥ በቀጥታ ግብይት ይፈጽሙባቸዋል።

የአሰራሩ መተግበር መንግስት ለገበያ በሚያቀርበው ቦንድ ላይ የዜጎች ፍላጎት እንዲጨምር ከማድረግም ባለፈ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶች ግዥ ላይ መሳተፍ ላልቻሉ ግለሰቦች አዲስ እድል ይፈጥርላቸዋል።

ከቦንድ ሽያጩ ከሚገኝ ወለድ ታክስ የማይከፈል ሲሆን፥ ይህም ተጠቃሚዊዎችን ወደ ገበያው የሚስብ ነው።

ዶክተር ዮሀንስ፥ ሁለተኛ ደረጃ የዋስትና ሰነዶች ግብይት ሲጀመር የተገዙ ሰነዶች አንድ ቦታ መቀመጥ አለባቸው ይላሉ።

ለጊዜው ብሄራዊ ባንክ ይህን ተግባር የሚወጣ መሆኑንና ግብይቱ ሰነድ መያዝ ሳያስፈልግ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ እንደሚፈፀም ነግረውናል።

የባንኩ ምክትል ገዥ ገበያውን ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ስጋቶችን መቆጣጠርና የኩባንያዎችን እምነት የማጎልበት ስራዎች በብሄራዊ ባንኩ ቢጀመርም ገበያው እየጎለበተ ሲሄድ ራሱን የቻለ ተቋም ይፈጠራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውሰጥ የሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ሰነዶች ግብይት አለመኖሩ እንደችግር ሲነሳ ቆይቷል ያሉት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው፥ በያዝነው በጀት ዓመት ወደተግባር ይገባል ብለዋል።

ለዓመታት የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀርቡበት የነበረው የሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ መጀመር የመንግስት የቦንድ ሽያጭን ያሳድግለታል።

የራሱ የገበያው መኖር በኢትዮጵያ አሁን ካሉት የንግድ ባንኮች በተጨማሪ የፋይናንስ አማራጭን ይፈጥራል።

ይህም ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብን የዋጋ ግሽበት በማይፈጠር መልኩ ለማዘዋወር እድልን ይፈጥራል።

ሁለተኛ ደረጃ ገበያውን ቀስ በቀስ ወደ ካፒታል ገቢያ ለማሳደግም እቅድ ተይዞለታል።

 


በንብረቴ ተሆነ