ሀገሪቱ ከሰሊጥ የወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) አዳዲስ የምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ በማድረግ ሀገሪቱ ከሰሊጥ የወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ፥ በሰሜን ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በጎንደር ግብርና ምርምር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን እና ኤስ ዲ ኤን በተባለ የኔዘርላንድስ ድርጅት የተመረቱ፣ በመስመር የተዘሩ እና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የተጠቀሙ የሰሊጥ ሰርቶ ማሳያዎችን ጎብኝተዋል።

ዶክተር እያሱ በጉብኝቱ ወቅት ሀገሪቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በግብርናው ዘርፍ ልታሳካው ለያዘችው ግብ የምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ ማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

የሰሊጥ የምርምር ውጤቶችን በመቀመርና ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሰራጭ ለማድረግም ሚኒስቴሩ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል።

ቡናን ጥራቱን በማረጋገጥ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድ የተገኙ ልምዶችን በሰሊጥም በመድገም ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ይሰራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

 

በክብረወሰን ኑሩ