የኢትዮጵያ የታክስ ጥናትና ምርምር ትስስር ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ዙሪያ ጥናትና ምርምር የሚያደርግ ብሔራዊ የታክስ ጥናትና ምርምር ትስስር ይፋ ተደረገ።

ዓለም ዓቀፉ የታክስና የልማት ማዕከል ከአሜሪካው ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው ትስስሩን ይፋ ያደረገው።

በትስስሩ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ተቋምና የእንግሊዙ ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት በአባልነት አቅፏል።

አገሪቱ በታክስ ላይ በተቋማትና በባለሙያች የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎችን የገንዘብና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የታክስ ሥርዓቱን ማዘመን የትስስሩ ዋና ተልዕኮ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም የሚሰሩት የምርምር ሥራዎች በኢትዮጵያውያን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በማከናወን የምርምር ውጤቶቹ ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውሉ ትስስሩ የድርሻውን እንደሚወጣ ተጠቁሟል።

ትስስሩ በሚያካሂዳቸው ዓውደ ጥናቶች፣ ስብሰባዎች እንዲሁም የምርምር ውጤቶች በታክስ ላይ ባለሙያዎች መረጃ እንዲለዋወጡ ከማገዙም በላይ በታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ላይ የሚሰሩ ተቋማትና ባለሙያዎችም በቅንጅት እንዲሰሩም ያግዛል ተብሏል።

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የገንዘብ ፖሊሲ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ አምሃ እንደተናገሩት ትስስሩ በገለልተኛ ተቋማት የሚካሄዱ ጥናቶች ላይ ምክክርና ውይይት እንዲካሄድ ያደርጋል።

ይህም በአገሪቱ ታክስ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትና ባለሙያዎች አቅማቸውን ለማጎልበት ያስችላል ብለዋል።

ትስስሩ ለመንግሥት በሚጠቅሙ የታክስ ዘርፎችና ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ጥናትና ምርምር ለማድረግ እድል ይሰጣል ያሉት አቶ መዝገቡ የአገሪቱን የታክስ ሥርዓት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

የዓለም ዓቀፍ ታክስና የልማት ማዕከል ዳይሬክተር ጊዩሊያ ማስካግኒ እንደተናገሩት ትስስሩ በአገሪቱ ያሉትን የታክስ ባለሙያዎች ለማቀናጀት ይረዳል።

በታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ከፍ እንዲልና አጠቃላይ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱ እንዲሻሻል በማድረግ ትሰስሩ ሚናው የጎላ እንደሚሆን ነው ያስረዱት።

በኢትዮጵያ ከአጠቃላዊ አገራዊ ምርት ውስጥ ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ 12 በመቶ ብቻ ሲሆን ይህም የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ከሚያስፈልገው በታች በመሆኑ የአገሪቱ የታክስ አሰባሰብ ሂደት መሻሻል እንዳለበት ይጠቁማል።

ምንጭ፦ ኢዜአ