ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የምርቶችን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መግታት ይገባል - የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የምርቶችን ህገ ወጥ እንቅስቃሴን መግታት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት የክልሉን የ2009 ኤክስፖርት ምርቶች አፈፃፀም እና የ2010 ዕቅድ ላይ የሚመክር ውይይት ከዞን አስተዳዳሪዎች እና መምሪያ ሀላፊዎች ጋር ባካሔዱበት ወቅት ነው።

በክልሉ በ2010 ዓ.ም 120 ሺህ ቶን ቡና፣ 5 ሺህ 434 ቶን ቅመማ ቅመም እና 10 ሺህ 286 ቶን ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዷል።

ወርቅ ከሚወጣባቸው ከቤንች ማጂ እና ሲዳማ ዞኖች 1 ሺህ 500 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙም ተገልጿል።

“በወጪ ንግድ ምርቶች እና ግብይት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ግድ የሚለን ጊዜ ነው" ያሉት አቶ ደሴ ዳልኬ፥ ይህ እንዲሆን ደግሞ በወጪ ንግድ ምርትና ግብይት ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለው ገቢ እንዳይገኝ ህገ ወጥ ንግድ ዋነኛ ማነቆ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፥ ችግሩን ለመፍታት በዘርፉ የተሰማራው አካል በቂ አመራር እየሰጠ አለመሆኑ ተገልጿል።

ለዚህም በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተገኙ ምርቶችን ከመውረስ ባለፈ በጥፋተኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይገባል ተብሏል።

ፓኬጅን አሟልቶ አለመተግበር እና የምርት ጥራት ችግር ከዘርፉ ተገቢው ጥቅም እንዳይገኝ እንቅፋት መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።

ለአብነትም ከከፍተኛ ቡና አምራቾች መካከል አንዱ በሆነው ሲዳማ ዞን ከ70 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ያረጀ የቡና ተክል መኖሩ የተጠቀሰ ሲሆን፥ በዚህ መልኩ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ስለማይቻል መሰል ማሳዎችን በአዳዲስ ተክሎች በፍጥነት መተካት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የክልሉ ዋነኛ ቡና አምራቾች በሆኑት ሲዳማ እና ጌድኦ ዞኖች ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ውርጭና አየር መዛባት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

በያዝነው ዓመትም በማዕከላዊ ዞኖች ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ የምርት መቀነስ ስለሚታይ እንደ ክልል ከ20 እስከ 30 በመቶ ምርት ሊቀንስ እንደሚችል በመስክ ጥናት መገመቱን በውይይቱ ወቅት የቀረበ ሰነድ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

በታደሰ ሽፈራው