የምርት ገበያው በነሃሴ ወር 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው ምርት አገበያይቷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በነሃሴ ወር ብቻ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የሚያወጡ ሰሊጥ፣ ቦሎቄና ቡና ማገበያየቱን ገለፀ።

የምርት ገበያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በአንድ ወሩ ውስጥ 33 ሺህ 528 ቶን ምርት አገበያይቷል።

በወሩ ካገበያያቸው ምርቶች መካከልም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚያወጣው ቡና ሲሆን፥ ከአጠቃላይ የግብይት መጠኑ ውስጥም ቡና በዋጋ 82 በመቶ እና በመጠን 63 በመቶ ይሸፍናል።

ወደ ውጭ የሚላከው የቡና ግብይት መጠንም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ66 በመቶ ጭማሪ እንዳለው በመግለጫው ተመልክቷል።

ለቡና ምርት ግብይት ያደገውም የምርቱን መገኛ እና ባለቤትነትን የተመረኮዘ የመኪና ግብይት ስርዓት በመካሄዱ መሆኑ ነው የተገለፀው።

ከቡና ቀጥሎ በሁለተኝነት ደረጃ ግብይት የተደረገው የሰሊጥ ምርት ሲሆን፥ 303 ሚሊየን ብር የሚያወጣ 11 ሺህ 479 ቶን ግብይት ተከናውኖበታል።