የኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ ያለፉት 10 ዓመታት ጉዞ ሲቃኝ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1999 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ሰባት አዳዲስ የንግድ ባንኮች ስራ ጀምረዋል።

ይህም ልማት ባንክን ጨምሮ ሀገሪቱ ያላትን የባንኮች ብዛት 18 አድርሶታል።

ነባሮች እና አዳዲሶቹ ባንኮች ከ10 ዓመት በፊት በመላ ሀገሪቱ የነበሯቸው 487 ቅርንጫፎች ብቻ ነበር።

ከሚሊኒየሙ የ10 ዓመታት ጉዞ በኋላ ግን የባንኮች ቅርንጫፍ ቁጥር 4 ሺህ 257 ደርሷል።

በእነዚህ ባንኮች የተቀመጠው የቁጠባ ገንዘብ በ1999 ዓ.ም 53 ነጥብ 8 ቢሊየን ከነበረበት አሁን ከ568 ቢሊየን ብር አልፏል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት 10 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ የ26 ነጥብ 8 በመቶ የቁጠባ እድገት ተመዝግቧል።

ከ10 ዓመታት በፊት 3 ሚሊየን የነበረው የባንክ ደብተር ባለቤቶች ቁጥር ወደ 26 ነጥብ 6 ሚሊየን ማድረስ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው እንደሚሉት፥ ይህ አሃዛዊ እድገት ህብረተሰቡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሳተፈ መምጣቱን ያሳያል።

የዚህ ድምር ውጤትም የኢትዮጵያ ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው 30 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አሁን 560 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አድርሷል።

ዶክተር ዮሐንስ ይህ የባንኩ ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ቦታ እንደሚያሳይ ጠቁመው፥ ይህ የሆነውም ባንኮቹ ካፒታላቸው በማደጉ ነው ይላሉ።

በሀገሪቱ ባንኮች በዚህ ደረጃ ሲያድጉ ከእድገታቸው በተቃራኒ ሊመጣባቸው የሚችለውን ችግር መቋቋም እንደቻሉም ነው ምክትል ገዥው የገለፁት።

በባንኮች እድገት ልክ ጤንነታቸውን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እያደጉ እንደሚመጡ ተናግረዋል።

የባንኮች መብዛት የተበዳሪን ቁጥር ስለሚያበዛ የማይመለስ የብድር ምጣኔን የማብዛት እድሉ ሊፈጠር ቢችልም፤ በኢትዮጵያ ግን በተቃራኒው መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች ያልተመለሰ ብድር ምጣኔ ካበደሩት 10 በመቶውን ያክል ነበር፤ ይህም ለንግድ ባንኮች ጤንነት መለኪያነት ከተቀመጠው የ5 በመቶ ያልተመለሰ ብድር ምጣኔ አንጻር አደጋ ውስጥ እንደነበሩ ያሳያል።

አሁን ላይ ግን በእጅጉ ተሻሽሎ የተበላሸ የብድር ምጣኔ 2 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ ይህም የዘርፉ እድገት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።

በእርግጥ በመስፈርቱ መሰረት የኢትዮጵያ ባንኮች ያልተመለሰ ብድር ምጣኔያቸው ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ቢሆንም፥ ይህ የባንኮችን ጤነኝነት ብቻ ነው የሚያሳየው ወይስ ብድርን ላለመስጠት ስጋትን መፍራታቸውን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

በሌላ በኩል ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መረጣ ስለሚያደርጉ ነው እዚህ ደረጃ የደረሱት የሚሉም አሉ።

የብሔራዊ ባንኩ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ፥ ባንኮች የአጭር ጊዜ ቀጠባን በሚሰበስቡበት ጊዜ ለመክፈል ረጅም ጊዜን የሚጠይቁ ብድሮችን መስጠት ችግር ይፈጥራል ብለዋል።

በሌላ በኩል የዛሬ 10 ዓመት የሀገሪቱ ባንኮች ከሚሰበስቡት ቁጠባ የሚበደራቸው እስከ ማጣት ደርሰው፥ 20 በመቶን ስለማያበድሩት በብሄራዊ ባንክ ከተቀመጠላቸው ግዴታ ያለፈ /excess reserve/ በባንኩ ይቀመጥላቸው ነበር።

አሁን ግን ባንኮች በዚህ መልኩ የሚያስቀምጡት ገንዘብ ከሰበሰቡት ቁጠባ ወደ ሁለት በመቶ መውረዱ እያበደሩ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ አንስተዋል።

የባንኮች ተደራሽነት አንዱ ቅርንጫፍ ለ148 ሺህ ሰዎች አገልግሎት ይሰጥ ከነበረበት ለ22 ሺህ ሰዎች እንዲሰጥ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

ይህ ዜጎችና ባንኮችን በደንብ ማቀራረብ መቻሉን ቢያሳይም፥ የሀገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከማጠናከር አንጻር ብዙ መሰራት እንዳለበት ይነሳል።

ከዚህ አንጻር ባንኮች በጊዜ ገደብ ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ካልሆነም እንዲዋሀዱ ይደረጋል ስለሚሉት ሁለት ሀሳቦች ዶክተር ዮሐንስ ካፒታልን የማሳደጉ ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ገዥው በምን ያህል መጠን የሚለው ግን በፖሊሲ የሚመለስ መሆኑን ከመናገር ያለፈ ሀሳብ ከመሰንዘር ተቆጥበዋል።

 

 

 

 


በካሳዬ ወልዴ