ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማገኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በተጠናቀቀው በጀት ዓመተ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማገኘቱን አስታወቀ።

ገቢው የተገኘው በበጀት ዓመቱ ከ2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ ሲሚንቶ አምርቶ ለገበያ በማቅረቡ መሆኑንም ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ገልጿል።

የፋብሪካው የሽያጭና ማርኬቲንግ ምክተል ስራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ አለማየሁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ ከተገኘው ገቢ ውስጥ ከ1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆነው ወደ ኬንያ እና ጅቡቲ ከተላከ ምርት ነው።

በዓመቱም በኢትዮጵያ የሚገኘው ፋብሪካ አፈፃፀም ከአፍሪካ ሀገራት ከናይጀሪያ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የፋብሪካውን ምርቶች ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመላክም የሲሚንቶ ናሙና መላኩን አቶ ታሪኩ ገልፀዋል።

የፋብሪካውን ገቢ ለማሳደግ በኦሮምያ ክልል ከ500 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ወጪ የተደረገበት እና በዓመት 120 ሚሊየን የሲሚንቶ ከረጢት ማምረት የሚችል ፋበሪካ ገንብቶ ማጠናቀቁንም አስታውቋል።

ፋብሪካው ከረጢቶቹን የሚያመርተው ሌሎች ሲሚንቶ ፋብሪካዎችንም ታሳቢ በማድረግ ሲሆን፥ ከ300 እስከ 500 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር ነው ተበሏል።

ማምረቻው ከዚህ ቀደም ከውጭ ይገባ የነበረውን ከረጢትና ይወጣ የነበረዉን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል ተብሏል።

 

በዙፋን ካሳሁን