በአማራ ክልል ባለፉት 10 ዓመታት 400 ሚሊየን ብር ያስመዘገቡ ዩኒየኖች ወደ ኢንዲስትሪ ልማት ተሸጋግረዋል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት 10 ዓመታት 400 ሚሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ዩኒየኖችና ሁለገብ የህብረት ስራ ማህበራት ወደ ኢንዱስትሪ ልማት መሸጋገራቸውን የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትልቅ ሰው ይታያል እንደገለጹት፥ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሳተፍ የጀመሩት 12 ዩኒየኖችና ሁለገብ የህብረት ስራ ማህበራት ናቸው፡፡

መርከብ፣ ዳሞት፣ ጎዛምን፣ ዘንባባ፣ እሪኩም፣ ፀሐይና ሌሎች ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማህበራት ወደ ኢንዱስትሪ ከገቡት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ዩኒየኖቹ 16 የዱቄት፣ የእንስሳት መኖ፣ የማርና የምጥን ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የዘይትና የሳሙና ማምረቻ ፋብሪካዎችን ገንብተው ወደ ማምረት ስራ በመግባት ለዘርፉ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን ወይዘሮ ትልቅ ሰው ተናግረዋል።

አራት ዩኒየኖችም የወተት ማቀነባበሪያና የከረጢት ማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ፥ በአዲሱ ዓመት ወደ ምርት እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

ስድስት ዩኒየኖችም ከ2005 ጀምሮ በየዓመቱ የተመረጡ የግብርና ምርቶችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ መሆናቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም ዩኒየኖቹ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ጥራቱን የጠበቀ የግብርና ምርት አርሶአደሩ እንዲያመርት የመካናይዜሽን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ መስጠት ጀምረዋል።

ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በተያዘው የበጀት ዓመት ተጨማሪ 28 ዩኒየኖችና ማህበራት የእርሻ ትራክተሮችና ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡ ይደረጋል።

እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ 15 ዩኒየኖችና 178 የህብረት ስራ ማህበራትን በተደራጀ መንገድ ወደ ኢንዱስትሪ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በክልሉ ከ10 ዓመት በፊት ከ315 ሚሊየን ብር ካፒታል ያላቸው 29 ዩኒየኖች የነበሩ ሲሆን፥ አሁን ላይ 847 ሚሊየን ብር ካፒታል ያላቸው 67 ዩኒየኖች መኖራቸው ታውቋል ።

ምንጭ፦ኢዜአ