ቢ ኤንድ ሲ አልሙኒየም ፋብሪካ የሀገር ውስጥ የአልሙኒየም ምርትን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ሊልክ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2009 (ኤፍቢሲ) ቢ ኤንድ ሲ አልሙኒየም ፋብሪካ የሀገር ውስጥ የአልሙኒየም ምርትን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ መላክ ሊጀምር ነው። 

ፋብሪካው ኢዳ ለተሰኘው የግብፅ የወጪ ገቢ ኩባንያ 28 ቶን የአልሙኒየም ምርትን ነው የሚልከው።

ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ከሀገር ውጭ በሚመጡ ግብአቶች ነበር ምርቱን የሚያመርተው።

አሁን ላይ ግን 80 በመቶ በሀገር ውስጥ ግብአቶች የተሸፈነ ሲሆን ኤክስፖርቱም እንደ ሀገር የመጀመሪያ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ በኋላም ምርቱን ለማምረት ከውጭ የሚመጡ ግብአቶች 20 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት የጎላ ሚና የሚጫወት መሆኑን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይማኖት አባተ ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

ዛሬ ምርቱን ወደ ግብፅ መላክ የሚጀምረው ኩባንያው በቀጣይ ሌሎች አገራትን የገበያ መዳረሻ ለማድረግ ማቀዱም ተመልክቷል።
ፋብሪካው በአመት ከ300 ቶን በላይ አልሙኒየም የማምረት አቅም አለው ።

 

በዙፋን ካሳሁን