በመዲናዋ በአዲስ ዓመት የዋዜማ ቀናት የባህል አልባሳት ግብይት ምን ይመስላል…

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2፣ 2009፣ (ኤፍ ቢ ሲ) የ2010 አዲስ ዓመት በዓል መቃረቡን ተከትሎ የሽሮ ሜዳና የሾላ ገበያዎች የባህል አልባሳትን በተለያየ ዋጋና በተለያየ የጥራት ደረጃ አቅርበው ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ናቸው።

በአዲስ ዓመት በዓል የዋዜማ ቀናት ከሚሸመቱ አልባሳት ውስጥ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የባህል አልባሳት ቀዳሚ ስፍራ አላቸው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በመጪው ሰኞ የሚከበረውን የዘመን መለወጫ በዓል አስመልክቶ የባህል አልባሳት ገበያ ምን እንደሚመስል ትናንት እና ዛሬ በሽሮ ሜዳና በሾላ ገበያዎች ቅኝት አድርጓል።

በቅኝቱም የባህል አልባሳት ገበያው ሞቅ ያለ እንደነበር መመልከት ተችሏል።

በሽሮ ሜዳ ገበያ የባህል አልባሳትን በመሸጥ የተሰማሩ ነጋዴዎች በተለያዩ ባህላዊ ጨርቆች እና የልብስ አሰራር ንድፎች ለአዋቂ እና ለህጻናት የሚሆኑ አልባሳትን አዘጋጅተዉ ገዥዎችን እያስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የ2010 አዲስ ዓመትን አስመልክቶም የባህል አልባሳቱን በአይነት እና በብዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባቸውን ነው የገለፁት።

በስፍራው የተገኙ ሸማቾችም በፈለጉት የልብስ አሰራር የተዘጋጁ አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሽሮ ሜዳ ገበያ በተለያየ የጥራት ደረጃ የተዘጋጁ የአዋቂ የባህል አልባሳት በሸሚዝ፣ በአላባሽና በሙሉ ቀሚስ ከነጠላው ጋር ከ150 ብር ጀምሮ ለገበያ ቀርበዋል።

የህጻናት አልባሳት ደግሞ ከ200 ብር ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ለሸማቾች ቀርበዋል።

ከአልባሳቱ ጋር አብረው የሚፈለጉ የወንዶች የባህል የቆዳ መጫሚያዎችም በተለያዩ ዲዛይኖች ከ200 ብር ጀምሮ፣ ለህጻናት ደግሞ ከ100 ብር ጀምሮ ዋጋ ተተምኖላቸው ግብይቱ ቀጥሏል።

የአንገትና የእጅ የባህል ጌጣጌጦች ከ40 እስከ 100 ብር በሆነ ዋጋ እየተሸጡ ነው።

በሾላ ገበያ አቅርቦቱና ግብይቱ እንደ ሽሮሜዳ ገበያ ሞቅ ባለ መልኩ እየተካሄደ ነው።

ዘንድሮ የባህል አልባሳት ዋጋ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የጨመረ መሆኑንን አስተያየታቸውን ለጣቢያችን የሰጡ ሸማቾች ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

 


በቤቴልሄም ጥጋቡ