በሞያሌና በነገሌ ቦረና ከተሞች ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞያሌና በነገሌ ቦረና ከተሞች በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ላይ በሃምሌ ወር በተደረገ ፍተሻ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ማግኘቱን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር የሺወርቅ ተጫነ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በሞያሌ በስድስት መኖሪያ ቤቶችና በነገሌ ቦረና በአንድ ቤት ላይ በተደረገው ፍተሻ የተለያዩ መድሃኒቶች ኤሌክትሮኒክስና አልባሳት ተገኝተዋል።

በሁለቱ ከተሞች በተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ የኦፕሬሽን ስራም ወደ መሃል ሀገር ሊገባ የነበረ ግምቱ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ኢንሱሊን የተሰኘ መድሃኒት፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ አዲስና አሮጌ አልባሳትና ኮስሞቲክሶችን መያዛቸውን ወይዘሮ የሺወርቅ አብራርተዋል።

በዚህ መልኩ ኮንትሮባንዱ በቤታቸውም ሆነ በተሽከርካሪዎቻቸው ውስጥ የተገኘባቸው ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡

 

 

 

 

በታሪክ አዱኛ