ኢትዮጵያ ከአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነች አይደለም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ በመስኖ የሚለማ መሬት ቢኖራትም አትክልትና ፍራፍሬን በሚፈለገው ደረጃ አምርታ መጠቀም አልቻለችም ተብሏል፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የአነስተኛ ሆልቲካልቸር ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ዋሌ ጌታነህ በርካታ አርሶ አደሮችን በዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰው፥ እስካሁን ግን የሚፈለገውን ያህል ውጤት አልተመዘገበም ብለዋል፡፡

አቶ ዋሌ ከ50 በመቶ በላይ የአቮካዶ ምርት ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ሜክስኮ በዘርፉ ያላት እምቅ ሀብት ከኢትዮጵያ ያነሰ መሆኑን ይናገራሉ።

ሆኖም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ በዓመት 500 ቶን የሚደርስ አቮካዶን ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው ኬንያ ጋር እንኳ መወዳደር እንዳልተቻለ ነው የገለፁት፡፡

ባለሙያው ዘንድሮ ከ11 ቶን በላይ አቮካዶ ከአርሶ አደሩ ማሳ በመሰብሰብ ለአውሮፓ ገበያ በማቅረብ ማስተዋወቅ እንደተቻለ አብራርተዋል።

የሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ ሰለሞን ዳኘ በበኩላቸው፥ ሀገሪቱ ያመረተችው አትክልትና ፍራፍሬ ለዓለም አቀፍ ገበያ በቂ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡

በሀገሪቱ ከሚመረተው አትክልትና ፍራፍሬ ውስጥ 99 ነጥብ 6 በመቶው ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውል ሲሆን ቀሪው ምርት ለጅቡቲ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን ነው አቶ ሰለሞን የጠቆሙት።

በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በሀገሪቱ ከተመረተው አትክልትና ፍራፍሬ አብዛኛው ምርት በአይነትና በጥራት ችግር ለዓለም ገበያ ሊቀርብ አልቻለም፡፡

አሁን ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ስትራቴጅ ተቀርፆ ወደ ተግባር መገባቱን የሚናገሩት የሚኒስተሩ ልዩ አማካሪ፥ የምርት ጥራትና ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን የመለየት ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ብቻ በ2008 ዓ.ም የተቀነባባረና ያልተቀነባበረ ከ94 ሺህ ቶን በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ማስገባቷን ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ ከ77 ሺህ ቶን በላይ የሸንኩርት ምርት ከሱዳን የምታስገባ ሲሆን፥ ለዚህም ከ15 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች።

የደቡብ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መለሰ አማና ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪና ለውጭ ገበያ የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን በመለየት በኩታ ገጠም ዘዴ ማልማት መጀመሩን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አይተነው እንደሻው በበኩላቸው፥ በክልሉ ለአትክልትና ፍራፍሬ ምቹ የሆኑ ወረዳዎች እንደተለዩ ገልፀዋል።

 

 


ተመስገን እንዳለ