የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት 523 ቢሊየን ብር መድረሱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ጠቅላላ ሀብት 523 ቢሊየን ብር መድረሱን የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የሀብት መጠናቸው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻፀር የ82 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ጭማሪ ማሳየቱን ነው ኤጀንሲው የገለፀው፡፡

በዚህም አፈፃፀሙ 101 ነጥብ 1 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንደገለፁት፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጠቅላላ ሀብት ከግማሽ ትሪሊየን ብር በላይ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነበረውን የሀብት ክምችት በ13 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በማሳደግ ከፋይናንስ ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት 89 ነጥብ 5 የሚሆነውን እንደሚሸፍን ዶክተር ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሀብት መጠን ከአጠቃላዩ 10 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑንም ነው የገለፁት።

የፋይናንስ ተቋማቱ በበጀት ዓመቱ 15 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገቡ ሲሆን፥ ከተያዘው እቅድ የ1 ቢሊየን ብር ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ከትርፉ ውስጥም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 95 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

ድርጅቶቹ ወደ ኢኮኖሚው ያሰራጩት የብድር መጠን የቦንድ ኩፖን ጨምሮ 99 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ ከተያዘለት እቅድ አንጻር 80 ነጥብ 6 በመቶ መሳካቱ ነው የተገለፀው፡፡

አጠቃላይ የቁጠባ ክምችቱም ወደ 365 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከፍ ማለቱ ተነግሯል፡፡

ከውጭ ንግድ እና ከሀዋላ ከሚገኝ ገቢም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 በነበረው ምንዛሪ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ እንዳገኙ ኤጀንሲው ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ ተቋማቱ በትርፋማነት፣ በቁጠባ፣ በብድር አሰጣጥና አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና ካሳ ክፍያ ያሳዩት አፈፃፀም ስኬታማ የሚባል ነበር ተብሏል፡፡

 

 

 

 

በራህዋ መብራህቱ