ከብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከእቅዱ ያነሰ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2009 በጀት አመት ከብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የወጪ ንግድ 75 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው ግን 47 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር መሆኑን የፌዴራል ብረታ ብረት እና ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስትቲዩት አስታወቀ።

ኢኒስትቲዩት የ2009 በጀት አመት አፈፃፀሙን ሲገመግም ነው ይህን ያለው።

ለአፈፃፀሙ ማነስ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት፣ በዋጋ፣ በጥራት እና በአቅርቦት ተወዳዳሪ አለመሆን በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

የገበያ ትስስር፣ የአስተዳደር እና የቴክኖሎጂ የአቅም ውስንነትም ኢንስቲትዩቱ እንደ ችግር አስቀምጧቸዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችም ያጋጣሟቸውን ችግሮች አንስክተዋል።

የቀረጥ ማስተካከያ ጥያቄ አለመመለስ፣ የምርት ጥራት ምዝና ሰርተፊኬት አለማግኘት፣ የትራንስፖርት ዋጋ ውድነት፣ የጥሬ እቃ ግብአት አቅርቦት ማነስ እና የመሳሰሉ ችግሮች ፈታኝ እንደሆኑባቸው ነው ባለሃብቶቹ የተናገሩት።

ከትራንስፖርት ውድነት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፥ ከ50 በመቶ በላይ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለሚልኩ ድርጅቶች እስከ 25 በመቶ የትራንስፖርት ቅናሽ እንደሚደሚያደርግ አስታውቋል።

ድርጅቱ የመረጃ ክፍተት እንጂ የትራንስፖርት ችግር የለም ብሏል።

ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እና መቆራረጥ፣ ከጉምሩክ የትራንስፖርት ችግሮች፣ በኢንቨስትመንት ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ የማድረግ ስራዎች በ2010 ኢንስቲትዩቱ በትኩረት እንደሚሰራባቸው አስታውቋል።

በ2009 በጀት አመት ከኬብል እና የሞባይል ምርቶች ከ44 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን፥ ከጌጣጌጦች፣ የቤት እቃ እና ማሽነሪዎች ደግሞ ከ3 ሚሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል።

 

 

 


በኤርሚያስ ፍቅሬ