ከወጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ጋሻው ታደሰ እንደገለጹት፥ በበጀት ዓመቱ ለማግኘት የታቀደው 4 ነጥብ 75 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን አፈጻጸሙ 61 ነጥብ 2 በመቶ ነው።

ይህ አፈፃፀም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ1 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከተገኘው ገቢ ትልቁን ድርሻ ከያዙት የግብርና ምርቶች መካከል ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት፣ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

በማምረቻና ማዕድን ዘርፎች ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኬሚካልና የግንባታ ግብዓቶች፣ ሞላሰስ፣ ታንታለም፣ ብረታ ብረትና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችም ወደ ውጭ አገራት ተልከዋል።

ቻይና፣ አሜሪካ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ሶማሊያ ደግሞ ምርቶቹ የተላኩባቸው ዋነኞቹ አገራት ናቸው።

የማምረቻው ዘርፉ ዕቅዶች አለመከናወን፣ የግብዓት ኦቅርቦት እጥረት እንዲሁም የማኔጅመንትና የቴክኒክ አቅም ውስንነት በወጪ ንግዱ አፈፃፀም ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸውን አቶ ጋሻው ጠቁመዋል።

በአንዳንድ ዘርፎች የኤክስፖርት ምርት አቅርቦት እጥረትና የጥራት መጓደል፣ የአብዛኛዎቹ የወጪ ንግድ ምርቶች የዓለም ገበያ ፍላጎት መቀዛቀዝና የህገወጥ ንግድ አለመገታት ለአፈፃፀሙ ዝቅተኝነት ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑም አስረድተዋል።

የማምረቻው ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ አለመቻሉም እንዲሁ።

በቀጣይ ለምርቶች መጠን፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት በመደገፍ፤ የተመረቱትም በወቅቱ እንዲወጡና ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግና ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተጀመረውን ሥራ በማጠናከር የወጪ ንግዱን በመጠንና በጥራት ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል።

የማምረቻው ዘርፉን የግብዓት አቅርቦት ችግር በማቃለል አስተዋፅኦውን በማሻሻል፣ አማራጭ ገበያዎችን በማፈላለግና ያለውን የገበያ ዕድል ለማስፋትም ጥረት ይደረጋል።

እነዚህን ስራዎች ለመከወን ባለድርሻ አካላትና የግብይት ተዋናዮችን በተሻለ ቅንጅት የመደገፍና የመከታተል ስራ ትኩረት ይሰጠዋል እንደ አቶ ጋሻው ገለፃ።

ባለድርሻ አካላት የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ እንዲያድግ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ