ለወጪ ንግድ የሚያግዙ ልዩ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለወጪ ንግዱ አጋዥ የሚሆኑ በአይነታቸው ልዩ የሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ጥናት እያካሄደ መሆኑን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ከጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበራት በቀረበ ጥያቄ በመነሳትና ወደ ውጭ የሚላኩ የቁም እንስሳትና ሌሎች ምርቶች ላይ የሚያጋጥመውን የምርት ጥራት መቀነስ ምክንያት በማድረግ ነው ጥናቱን እያካሄደ ያለው።

በባለስልጣኑ የጭነት ትራንስፖርት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ወልዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እንደየጭነት አይነታቸው የተለዩ ተሽከርካሪዎች ባለመኖራቸው ወደ ውጭ የሚላኩ ሸቀጦች ጥራት እንዲቀንስና የደረጃ መውረድም እንዲያጋጥም ምክንያት ሆኗል።

በመሆኑም ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለቁም እንስሳት ማጓጓዣ የሚያገለግሉና ወደ ወደብ ለማድረስ የሚያግዙ ልዩ ተሽከርካሪዎችን በግዢ ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሆነ አመልክቷል

ባለሃብቶችና የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበርም ለመሳተፍ እያሳየ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ባለስልጣኑ ጥናቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ትግበራው የሚገባ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በትእግስት ስለሺ