ባለፉት ሶስት ወራት የቡና የወጪ ንግድ መነቃቃት አሳይቷል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቡና ግብይቱ ላይ የአሰራር ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ባለፉት ሶስት ወራት የቡና የወጪ ንግድ መነቃቃት አሳይቷል።

የቡና እና ሻይ ልማት እና ግብይት ባለስልጣን፥ ባለፉት ሶስት ወራት ለአለም ገበያ ለማቅረብ ካቀደው የ20 በመቶ ጭማሬ ያለው ቡና ለአለም ገበያ አቅርቤያለሁ ብሏል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር፥ የመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላት አሉታዊ ጎናቸው አመዝኗል፤ ያስከተሉት ጉዳትም ቀላል አይደለም ብለዋል።

በየመንደሩ እየዞረ ቡና የሚሰበስብ ደላላ መበራከት፣ በኮሚሽን የሚሰሩ ወኪሎች መፈጠር እና እሸት ቡና ከተለቀመ በ24 ሰአት ጊዜ ወደ ኢንዱስትሪ ማድረስ አለመቻሉ ለህገወጥ ንግድ እና ዝውውር መንስኤ መሆኑንም አንስተዋል።

ባለስልጣኑ የዘረጋው የአሰራር ማሻሻያም የቡና ግብይት በማጠቢያና በመቀሸሪያ ኢንዱስትሪዎች ማካሄድ፣ ኢንዱስትሪዎች በሌሉበት ፣ ርቀት ባለበት ወይም በከተማ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ አማካኝ በሆነ ቦታ ግብይቱ እንዲካሄድ የሚያደርግ መሆኑን ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የሚናገሩት።

አሰራሩ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን የገለጹት አቶ ሻፊ፥ የተመረተው ቡና በጥራት ለውጭ ገበያ የሚቀርብበትን መንገድም ያመቻቻል ብለዋል።

እነዚህ የአሰራር እና የህግ ማሻሻያዎች ከተደረጉ በኋላ በቡና የወጪ ንግድ ላይ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና በመጠንም በገቢም ጭማሪ ማሳየቱንም ነው ያነሱት።

በበጀት አመቱ ካለፉት አመታት በ75 ሺህ ቶን የበለጠ ቡና ለውጭ ገበያ የቀረበ ሲሆን፥ ባለፉት ሶስት ወራትም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ27 ሺህ ቶን የሚበልጥ ቡና ተልኳል ብለዋል።

የአሰራር ማሻሻያው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ያነሳው ባለስልጣኑ፥ ባለፈው ሰኔ ወር የፀደቀው የቡና ግብይት አዋጅም የቡና ወጪ ገቢውን ይበልጥ ለማሳደግ ይስችላል ብሏል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትለከው ምርት25 በመቶውን ገቢ የምታገኘው ከቡና ምርት መሆኑን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 


በተመስገን እንዳለ