የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ሊሰማሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 7፣ 2009 ( ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ባለሀብቶች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በአዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደሚሰማሩ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ሚስተር ፋቲህ ዩሉሶይ አስታወቁ።

በአሁኑ ወቅት ቱርክ በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኢንቨስትመንት እያከናወነች ትገኛለች።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩት ድርጅቶች 165 ሲሆኑ፥ አብዛኛዎቹ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

አምባሳደር ፋቲህ እንደተናገሩት፤ የቱርክ ባለሀብቶች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በግንባታ ግብዓቶች፣ በቤትና ቢሮ ቁሳቁሶች፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በታዳሽ ሀይል፣ በግብርና፣ በማዕድን ቁፋሮና በትምህርት ዘርፎች ይሰማራሉ።

ቱርክ በአፍሪካ ከምታከናውነው ኢንቨስትመንት ከፍተኛው መጠን የሚገኘው በኢትዮጵያ ሲሆን፥ ይህም በሃገሪቷ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመኖሩ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ከኦቶማን ተርክሽ አገዛዝ ጀምሮ ቢሆንም፥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ግን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1926 ቱርክ ስድስተኛ ሃገር በመሆን በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በከፈተችበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 


ምንጭ፡- ኢዜአ