የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን በ2009 የበጀት ዓመት 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ እንደገለፀው በበጀት ዓመቱ 12 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም ከዚህ ውስጥ 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብቻ ነው የተሰበሰበው።

ባለሰልጣኑ ካቀደው ገቢ አንጻር 86 ነጥብ 9 በመቶውን ማሳካቱን ጠቁሟል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ በሰጡት መግለጫ ከተገኘው ገቢ መካከል ከተቀጣሪዎች 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ ከነጋዴዎች 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር እንዲሁም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብሩን ከአርሶ አደሩ ተሰብቧል ብለዋል፡፡

አቶ አህመድ ቀሪው ገቢ ደግሞ ከማህበራዊ አገልግሎት የተገኘ መሆኑ ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲናጻጸር በ20 ሚሊየን ብር ቅናሽ አሳይቷል።

ግብር ከፋዩ በወቅቱና በተገቢው መንገድ ግብሩን አለመክፈሉና ለሚፈጸም ግብይት ደረሰኝ አለመስጠት ገቢው ከባለፈው ዓመት አንጻር ላሳየው ቅናሽ በምክንያትነት ተቀምጧል።

 

 

 

 


በሙሉጌታ ተረፈ