ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሀገሪቱን ለውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሀገሪቱን ለውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጉ ነው።

ሀገሪቱ በአፍሪካ በተለይ በአነስተኛና መካከለኛ ማምረቻ ዘርፍ ከፍተኛ መጠን ያለውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የማክ ኪንሲ ግሎባል ጥናት ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዲሁም በቆዳ ዘርፍ ተወዳዳሪነቷ ከፍ ለማለቱ የሰው ሃይል አቅርቦት ምቹነትን እንደ አንድ ምክንያት ያስቀምጣል።

በኢትዮጵያ አንድ ቲሸርት ለማምረት ለአንድ ሰው የሚወጣው የጉልበት ክፍያ 0 ነጥብ 14 የአሜሪካ ዶላር ነው።

ይህ መጠን በጨርቃ ጨርቅ ምርታቸው በሰፋት ከሚታወቁት ቬትናምና ቻይና ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በታች ያንሳል።

ሃገሪቱ ወደ አለም አቀፍ ገበያ የምታቀርባቸው ሰፊ የሰው ሃይልን የሚጠይቁ ምርቶች መጠንም ከ10 አመታት በፊት ከነበረው በእጀጉ ከፍ ብሏል።

እነዚህ ሁሉ ለውጦች ግን ከሃገሪቱ አቅም አንፃር በቂ አይደሉም ይላሉ ከ45 አመት በላይ በፋይናንስ ዘርፍ ዙሪያ የሰሩት ፕሮፌሰር ፍሰሃፂዩን መንግስቱ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ከሆነ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ 20 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 130 ባለሃብቶች የኢንቨስትመነት ፈቃድ ወስደዋል።

ከእነዚሀ መካከል 101 የሚሆኑት በቀጥታ የውጭ ኢነቨስትመንት ለመሳተፍ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ኩባንያዎች ናቸው።

በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨሰትመነት ወደ ሃገር የሚገባው መዋዕለ ነዋይ ያለው በርካታ ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ ጥራት ያለውን ኢንቨሰትመንት በመሳብ በኩል ግን አሰቀድመው ከግምት ሊገቡ የሚገባቸው ሁኔታዎች አሉ ይላሉ ፕሮፌሰር ፍሰሃፂዩን።

የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተሰጠው ትኩረት ልክ ኢንቨስተሮች በገቡት ቃል መሰረት ኢትዮጵያውያንን የአዳዲስ ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ አሰራር እውቀት ባለቤት ማድረግም ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል።

የእውቀት ሽግግሩ መፈፀም ባለበት ልክ መፈጸሙ የሚለካበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚገኘውን መዋዕለ ነዋይ ከሃገሪቱ ኦኮኖሚ ጋር ለማስተሳሰርና ሀገሪቱም ከኢንቨስትመንቱ በሚባለው ልክ እንድትጠቀም ለማድረግ ደግሞ በካፒታል፣ በስራ ዕድልና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ተጨባጭ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰር ፍሰሃ ፂዩን ያነሱት።

የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አደማሱ ነበበ በበኩላቸው፥ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት ሀገሪቱ በሁለተኛው የእድገት እና ትራስፎርሜሽን እቅድ ግቦች በማሳካት እና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ይለካል ብለዋል።

በዚህም ለቀላል አምራች ተቋማት የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እያንዳንዳቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የስራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ መሆናቸው ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፒም ቫን ባልኩም፥ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት በሚሰራበት ሃገር ውስጥ ያለውን የሰራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በሚያበረክተው አስተዋፅኦ ይለካል ብለዋል።

 

 

 


በሰላማዊት ካሳ