ወደ ውጭ ከተላከ ቡና 866 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላከ ቡና 866 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታውቋል።

እንደ ባለስልጣኑ ገለጻ በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ለማግኘት ከተያዘው እቅድ ውስጥ 92 በመቶውን ማሳካት ተችሏል።

በዘንድሮው ዓመት የተገኘው ገቢ እና የተላከው የቡና መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

ወደ ውጭ የተላከው የቡና መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ11 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፥ የተገኘው ገቢም በ20 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገልጿል።

በባለስልጣኑ የገበያ ልማት እና ማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳኒሶ፥ የኢትዮጵያ ቡና ከ60 ወደሚበልጡ ሀገራት እንደሚላክ ገልፀዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ግን የኢትዮጵያን ቡና ወደ ሀገራቸው ያስገቡት ሀገራት ቁጥር 57 ናቸው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

86 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ቡና ወደ ሀገራቸው ካስገቡ ሀገራት ውስጥም ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ሱዳን እና ደቡብ ኮሪያ ይገኙበታል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላከው ቡና ውስጥ ጀርመን ብቻ 18 በመቶውን መግዛቷንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ