የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አገልግሎት አይሰጥም

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 4 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በእድሳት ላይ ሚገኘው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አገልግሎት እንደማይሰጥ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ደረጃ ማሻሻልና ተደራሽ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በዚህም በጠጠር ደረጃ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኮንክሪት አስፓልት እንዲያድግ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተካሄደ ባለው የእድሳት ሥራ ምክንያትም ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አውሮፕላን ማረፊያው አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ ተጓዦች የኮምቦልቻንና መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በአማራጭነት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የሰመራ አውሮፕላን ደረጃውን የጠበቀ የመንገደኞች ማረፊያ ተርሚናል ግንባታ ሥራ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ ይገኛል።

አሁን ላይም 20 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ክልሉ በቀጣይ ዓመት ለሚያስተናግደው 12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል መድረስ በሚያስችለው ቁመና ላይ ይገኛል ተብሏል።

ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የአውሮፕላን መንደርደሪያ ኮንክሪት አስፓልት፥ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር ስፋት አለው።

ከአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳው ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ቀሪው የአውሮፕላን መንደርደሪያ የመጀመሪያ ደረጃ አስፓልት መልበሱን አቶ ወንድም አመልክተዋል።

ቀሪ ሥራዎችን በቀጣዮቹ 21 ቀናት ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ አውሮፕላን ማረፊያው ሥራውን እንዲጀምር ይደረጋልም ብለዋል።

አውሮፕላን ማረፊያው ደረጃ የማሳደግ ስራው ሲጠናቀቅ፥ አሁን እያስተናገደ ከሚገኘዉ "Q-400" አውሮፕላን በተጨማሪ "ቦይንግ 737" አውሮፕላኖችን ማስተናገድ ይችላል።

የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ በታህሳስ 2006 ዓ.ም ስራ መጀመሩን ይታወሳል።