የካንቤቢ ዳይፐር አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ በይፋ ማምረት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣2009 (ኤፍ. ቢ. ሲ) ግዙፉ የካንቤቢ ዳይፐር አምራች የሆነው የቱርኩ ኦንቴክስ ኩባንያ በኢትዮጵያ የምርት ስራ መጀመሩን ይፋ አደረገ፡፡

በዓመት 250 ሚሊየን ዳይፐር የሚያመርተው ኦንቴክስ ኩባንያው በአፍሪካ የመጀመሪያው የዳይፐት ምርቱ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በምርቱም ኢትዮጵያ ዳይፐር ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል ነው የተባለው፡

ከምርቱ መካከልም 40 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን የሚያቀርብ ሲሆን 60 በመቶው ደግሞ ወደ ውጭ ገበያ የሚላክ ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከባንያው ከሚጠበቅበት 60 በመቶውን ብቻ እያመረተ ሲሆን፥ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት እንደሚገባ ነው የተነገረው፡፡

በዛሬው ዕለት በተደረገው ይፋ የምርት ማስጀመር ሂደት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ እቁባይ፥ ኩባንያው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የእድገት ጉዞ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ዶክተር አርከበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉ ቆይታ፥ ኦንቴክስ የዳይፐር አምራች ኩባንያ በፈረንጆቹ 2020፥ 400 ሚሊየን ዩሮ የሚገመት ዋጋ ያለው ምርት እንደሚያመርት ነው የጠቆሙት፡፡

ኩባንያው በቴክኖሎጂ የዕውቀት ሽግግር ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

እየተመረተ ከሚገኘው ካንቤቢ ዳይፐር መካከል በሞያሌ አድርጎ ለኬንያ ገበያ እንደሚቀርብም ነው ዶክተር አርከበ የተናገሩት፡፡

ኩባንያው ለምርት ከውጭ ከሚያስገባው ግብዓት ውስጥ 40 በመቶው በሀገር ውስጥ እንዲቀርብ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቻርልስ አዚዝ በበኩላቸው፥ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የዳይፐር ምርት እንዲጀምሩ መንግስት ለፈጠረው ምቹ ሁኔታ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከህጻናት ዳይፐር ባሻገር ለአዋቂዎች እና ለሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንደሚያመርቱም ነው የገለጹት፡፡

ኩባንያው አሁን ላይ በደቂቃ በአማካይ 700 ዳይፐሮችን እያመረተ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 18 ኩባንያዎች የተሰማሩ ሲሆን ስድስቱ ጨርቃጨርቅ በማምረት ምርታቸ|ውን ለውጪ ገበያ እያቀረቡ ነው፡፡

 

 

 

በታሪክ አዱኛ