የኬኛ ቤቬሬጅ ፋብሪካ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎችን በአባልነት የያዘው የኬኛ ቤቬሬጅ አክሲዮን ማህበር የፋብሪካ ግንባታ በጊንጪ ወረዳ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ ይህ ፕሮጀክት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና እንደጅምር የሚወሰድ ነው ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ እና የንቅናቄው ሰብሳቢ አቶ አባ ዱላ ገመዳ በበኩላቸው፥ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችና በሺህ የሚቆጠሩ አርሶና አርብቶ አደሮችን በአባልነት የያዘ አክሲዮን በመሆኑ ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው ብለዋል።

እጅ ለእጅ ተያይዞ ሁሉንም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ፥ ሌሎች በአማራጭ የተያዙ አክሲዮኖችም ወደ ተግባር መግባታቸውን አንስተዋል።

በ100 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን ለማስጀመር የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ኬኛ ቤቬሬጅ፥ ለግንባታው ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተመድቦለታል።

በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በመጀመሪያ ዙር በዓመት 2 ሚሊየን ሄክቶ ሊትር መጠጦችን ያመርታል።

ኬኛ ቤቬሬጅ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑም ተጠቁሟል።