በእደ ጥበብ ውጤቶች ላይ ከውጭ የሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገሪቱ እምቅ አቅም የሆኑት የእደ ጥበብ ውጤቶች ከውጭ ሀገራት በሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ተፅእኖ ስር እየወደቁ መሆናቸውን በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ይናገራሉ።

ነጋዴዎች እና ተጠቃሚዎች በሰጡት አስተያየት፥ ኢትዮጵያ ለዘመናዊ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርት የሰጠችውን ትኩረት ያህል የሽመና ውጤቶችን መመልከት አልቻለችም ብለዋል፡፡

ከእደ ጥበብ ውጤቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የባህል ልብስ ለኢትዮጵያ የሀገር ባህል አልባሳት ከልብስም በላይ፥ የሀገሪቱ ህዝቦች የተለያየ ማንነት መገለጫ ነው።

ከዚህ በላይም በርካታ የስራ እድልን መፍጠር የሚያስችል ትልቅ አቅም ያለው ዘርፍ እንደሆነም ይነገራል፤ ይሁን እንጅ ዘርፉ ከባድ ፈተና ተጋርጦበታል።

ችግሩ ከፈትል ስራ እስከ ሽመናና የመጨረሻው የምርት ደረጃ ድረስ ለተሰማሩ ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው፥ የህልውና ስጋት ምንጭ መሆኑንም ባለሙያዎች እና ነጋዴዎች ያነሳሉ።

ከውጪ ሀገራት የሚገቡት ተመሳሳይ ምርቶች ከሚመጡበት ሀገር የኢኮኖሚ አቅም መጠንከር እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤትነት አንጻር፥ የሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ተፅእኖ እያሳደሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ለሀገር ውስጥ ምርት የሚያስፈልገው ግብዓት ከውጪ የሚመጣ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ፥ የሀገር ውስጥ አምራቹን እና ምርትን የመወዳደር አቅም እንዳዳከመው አስረድተዋል።

ለዚህም ከእስያ ሀገራት በተለይም ከቻይና የሚገባው ከጥለት እስከ መነን ብትን የባህል ጨርቅ ዋጋን ሰብሮ የሚገባ በመሆኑ፥ ተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ምርቶችን እየተጋፋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከውጪ የሚገባ አንድ ሜትር መነን ጨርቅ አስራ ስድስት ብር ሲሸጥ፥ በኢትዮጵያ የሚመረተው ደግሞ እስከ 45 ብር ዋጋ አለው።

የቻይናዎቹ የማምረት አቅም ከኢትዮጵያኖቹ እጅጉን የራቀ በመሆኑ፥ ከብዛት ትርፍ ለማግኘት በቅናሽ ዋጋ ገበያውን ይሞሉታል።

አስተያየት ሰጭዎቹም የሽመና ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ማብቃት እና የአሰራር ስርዓቱን ማዘመን፥ የፈጠራ ክህሎታቸውንም ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይገልጻሉ።

ከዚህ ባለፈም በዘመናዊ መልኩ የባህል አልባሳቱ በፋብሪካ ደረጃ እንዲመረቱ ማስቻልን፥ እንደ ዘላቂ መፍትሄም ይጠቁማሉ።

የሀገር ውስጥ ምርቶች ከቻይና ከሚመጡ ምርቶች በገበያ ውስጥ በብዛት መኖራቸውን በመጥቀስም፥ መንግስት ይህንን አጥንቶ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ፥ ዘርፉን ከውጭ ሀገር ምርት ወረራ ለመታደግ ከውጪ ሀገር የሚገቡ አልባሳት ላይ 35 በመቶ ቀረጥ መጣሉን ገልጿል።

በባለስልጣኑ የዋጋ ትመናና ታሪፍ ምደባ አሰራርና ልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ በቀለ እንደተናገሩት፥ ችግሩ በዚህ ልክ መከሰቱ እንደማይታወቅ እና አስፈላጊ ከሆነ ቀረጡን እስከማሻሻል ሊደረስ እንደሚችል ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲቲዩት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባንትይሁን ገሰሰ፥ ዘርፉ በአለም አቀፍ ደረጃ የባለቤትነት መብት እና እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ኢንስቲቲዩት ዘርፉንና ባለሙያውን ከማዘመን ባሻገር እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች መቅረፍ በሚያስችል ደረጃ ምርቱ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከኢንዱስትሪ ፓርኮቸ ግንባታ ጋር ተያይዞ ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል።

ከዘርፉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ50 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 


በቤተልሄም ጥጋቡ