የኳታሩ ኤዝዳን በአዲስ አበባ በሪልስቴት ለመሰማራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የኳታሩ ኤዝዳን ሆልዲንግ ግሩፕ ኩባንያ በአዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ የግንባታ ዘርፍ ማከናወን የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

የመግባቢያ ስምምነቱን የኩባንያው ሊቀ መንበር ሼክ ዶክተር ካሊድ ቢን ታኒ ቢን አብዱላህ አል-ታኒ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ኩባንያው በከተማዋ 60 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልን ጨምሮ፥ ደረጃውን የጠበቀ የስብሰባ ማዕከል፣ ሆቴል አፓርትመንቶች፣ የገበያ ማዕከል እና ዘመናዊ ምግብ ቤቶችን ለመገንባት ያስችለዋል።

በስምምነቱ ወቅት የኩባንያው ሊቀ መንበር፥ ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማገዝ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያቸው የሆነው ኢንቨስትመንትም ስኬታማ ይሆናል ሲሉም ነው የተናገሩት።

ፕሮጀክቱ በታቀደው መሰረት ወደ ስራ እንዲገባ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል።

eZDAN_2.jpg

ከስምምነቱ ቀደም ብሎ የኩባንያው ሊቀ መንበር በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጉብኝት በማድረግ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል።

የኩባንያው ምክትል ሊቀ መንበር ሼክ አብዱላህ ቢን ታኒ አል-ታኒ እና የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊ ሞሃመድ የተመራ ልዑክም፥ በአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር የኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ፥ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር።

ኢሚሩ በጉብኝታቸው ወቅት በሃገራቱ መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ማስገባት በሚቻልባቸው አግባቦች ዙሪያ መክረዋል።

ጉብኝቱ ሃገራቱ በተለይም በንግድ እና ኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ እና በኳታር መካከል ያለውን፥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ እንደነበርም ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት አውድ እና የሃገሪቱ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆን፥ የሃገራቱን ግንኙነት በኢንቨስትመንት መስክም ማጠናከር እንደሚያስችል ታምኖበታል።

መረጃው የኳታሩ ፔኒንሱላ የዜና ምንጭ ነው።