4 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) አራት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ ግል ለማዘዋወር እየሰራ መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው፥ እስከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ወደ ግል እንዲዘዋወሩ ይደረጋሉ ከተባሉት የልማት ደርጅቶች መካከል ሸበሌ ትራንስፖርት አንዱ ነው።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማህበር እና አዳሚ ቱሉ ጸረ ተባይ ማዘጋጃ ይገኙበታል።

ሚኒስቴሩ በአሁን ወቅት የልማት ድርጅቶቹን ወደ ግል ለማዞር በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ወደ ግል ይዞታ ከተዘዋወሩ የልማት ድርጅቶች ከ12 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱም ተመልክቷል።

በታሪክ አዱኛ