በምዕራብ አርሲ ዞን ለስራ አጥ ወጣቶች 24 የእርሻ ትራክተሮች ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ አርሲ ዞን በ24 ማህበራት ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች 24 የእርሻ ትራክተሮች ድጋፍ ተደረገላቸው።

ትራክተሮቹ በዞኑ የስራ እድል ፈጠራ እና የከተሞች ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት አማካኝነት ተገዝተው ለወጣቶቹ የተላለፉ ናቸው።

የፅህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ደስታ ፈይሳ እንደተናገሩት፥ 26 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የወጣባቸው ትራክተሮች በማህበራት ለተደራጁ 202 ወጣቶች የተሰጡ ናቸው።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ከፍያለው የትራክተሮቹን ቁልፍ ለወጣቶቹ አስረክበዋል፡፡

የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች በበኩላቸው፥ መንግስት ስራ አጥነትን ለመቅረፍ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።

ነዋሪዎቹ በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎች የሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ መጓተት፥ ወጣቶች በታቀደው መሰረት ወደስራ እንዳይገቡ እያደረጋቸው በመሆኑ ሊቀረፍ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፍያለዉ አያና፥ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥቆማዎችን በመቀበልና ችግሮቹን በመፍታት ወጣቶቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።


መረጃውን የሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም ባልደረባችን ቢቂላ ቱፋ አድርሶናል።