የመጀመሪያው የኢትዮ - አልጀሪያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአልጀሪያ ኩባንያዎች የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የገበያ መዳረሻዎችን ለመጠቀም ኢትዮጵያ ትክክለኛዋ አገር መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመጀመሪያው የኢትዮ-አልጀሪያ የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፥ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እድሜ ያለው የኢትዮ- አልጀሪያ ግንኙነት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተወስኖ ቆይቷል።

ይህን ግንኙነት ወደ ሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለመቀየር ሁለቱ አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው ያሉት ዶክተር አክሊሉ፥ ተደራራቢ ቀረጥን ማስቀረት፣ የኢንቨስትመንት ጥበቃ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህልና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ስምምነት ተፈራርመናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ባላት ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለአልጀሪያ ባለሃብቶች ምቹ መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ኢትዮጵያም ምርቶቿን ወደ አውሮፓ ገበያዎች ለመላክ አልጀሪያ ጥሩ መሸጋገሪያ እንደምትሆናት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአለማችን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፥ የእርሻ ማቀነባበሪያ፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ የመድሃኒት፣ የጨርቃ ጨርቅ ልማትና ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአልጀሪያ ኤምባሲ ተወካይ ሚስ አፌፍ ቡቶባ በበኩላቸው፥ ሁለቱ አገራት የነበራቸውን ጠንካራ የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚ ትስስር መቀየር የሚያስችላቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሁለትዮሽ ቢዝነስ ፎረምና ሌሎች ስራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ በአልጀርስ ኤምባሲዋን መክፈቷ፣ የአዲስ አበባ - አልጀርስ ቀጥታ በረራ አገልግሎትና የአገራቱ ከፍተኛ መሪዎች ያደረጓቸው ጉብኝቶች ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያልም ነው ያሉት።

በሁለትዮሽና አለም አቀፍ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የቆየው የኢትዮጵያና አልጀሪያ ወዳጅነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማደግ ላይ ሲሆን፥ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት ዜሮ የንግድ ልውውጥ አሁን የ8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ዕድገት አሳይቷል።

የኢትዮ-አልጀሪያ ቢዝነስ ፎረም የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች የምርትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የአልጀሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ተብሏል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ