የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ከ158 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ158 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።

የአክሲዮን ማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አዱኛ አፈወርቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥

ከጠቅላላ ገቢው ውስጥ ከ39 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ለውጪ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ነው።

በዘጠኝ ወራቱ ፋብሪካው ከ3 ነጥብ 9 ሚሊየን ሜትር በላይ ጨርቅ እና ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ኪሎ ግራም በላይ ክር ያመረተ ሲሆን፥ ከ805 ሺህ በላይ ጥንድ አንሶላዎች ተመርተው ለሸያጭ መቅረባቸውንም አቶ አዱኛ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባደረገው ክትትል እና ድጋፍ 70 በመቶ የነበረው የፋብሪካው ምርቶች ጥራት ወደ 90 በመቶ ከፍ ማለቱንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ማህበሩ የፋብሪካውን የማምረት አቅም እና ገቢውን ለማሳደግ 10 የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመለየት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ጋር ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት መጨረሱንም ሃላፊው ተናግረዋል።