በቡና የገበያ ሰንሰለት ላይ ሊደረግ የታሰበው ማሻሻያ ተስፋ ተጥሎበታል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቡና ምርቷ ከአለም አምስተኛ ደረጃን የያዘችው ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ማሻሻያ ለማድረግ አቅዳለች።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ከፋይናንሺያል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሀገሪቱ ቡና በጨረታ ለገበያ የሚቀርብበትን አሰራር በማስተካከል እና ህገወጥ የቡና ንግድን በመቀነስ ነው ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ያቀደችው ብለዋል።

ከኮሎምቢያ የተቀመረው ልምድ ሀገሪቱ ከቡና የወጪ ንግድ የምታገኘውን አመታዊ የውጭ ምንዛሬ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ልዩ አማካሪው የተናገሩት።

አዲሱ ማሻሻያ በዋናነት የቡና ምርቶችን መገኛ እና ሌሎች መረጃዎችን የተሟላ በማድረግ እና ጥራት ያለው ምርት እንዲኖር ሁኔታዎችን በማመቻቸት የባለ ልዩ ጣዕም ቡናን ለአለም ገበያ ማቅረብ ላይ ያተኩራል።

“አዲሱን ማሻሻያ በአግባቡ ተግባራዊ ካደረግን አሁን እያገኘን ካለነው አምስት እጥፍ ገቢ ማግኘት እንችላለን” ያሉት ዶክተር አርከበ፥ ለገበያ የሚቀርብ ቡና የተሟላ መረጃ እንዲኖረው፣ የገበሬዎችን ምርታማነት የሚያሳድጉ ማበረታቻዎችን መዘርጋት እና የቡና ማሳዎች ማስፋፋት የማሻሻያው ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

የአለም የቡና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ባለፈው አመት 400 ሺህ ቶን ቡና ያመረተች ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ግማሹን ለውጭ ገበያ አቅርባለች።

ህገወጥ የቡና ንግድን መቆጣጠር ቢቻልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች የአሰራር ክፍተቶች ቢታረሙ ግን የሀገሪቱን አመታዊ የቡና የወጪ ንግድ አሁን ካለበት በ50 በመቶ ማሳደግ ይቻል እንደነበር ነው ዶክተር አርከበ ያነሱት።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2008 ተደርጎ በነበረው ማሻሻያ የሀገሪቱ የቡና ምርት በኢትዮጵያ የምርት ገበያ በኩል ነበር ለገበያ የሚቀርበው። በአዲሱ ማሻሻያ ግን ይህ የምርት ገበያው ሚና እንዲቀር የሚል ሀሳብ ማካተቱን አዲስ ፎርቹን በቅርቡ ዘግቧል። ማሻሻያው በቡና ምርት ላይ እሴት የሚጨምሩ ኩባንያዎች ቡናን ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ ይችላሉ ይላል።

ይህም የቡና ምርቶችን መረጃ (የተመረቱበት ቦታ እና አይነት) ለማወቅ አዳጋች በመሆኑ በባለ ልዩ ጣዕም ቡና ገበያው ላይ ሳንካ መፍጠሩ ይነገራል።

በአዲሱ ማሻሻያ እያንዳንዱ የቡና ምርት ለጨረታ ቀርቦ እስኪሸጥ ድረስ ለየብቻ ተለይቶ እንዲቀመጥ የሚደረግ ሲሆን፥ ሙሉ መረጃቸውም ይመዘገባል።

ማሻሻያው የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ቡና አምርተው ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉም እድል ፈጥሯል።

ከቡና ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚያከናውኑ ተቋማትም በአንድ ጣሪያ ስር እንዲሰባሰቡ ይደረጋል ነው የተባለው።

የኔዘርላንዱ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና አቅራቢ ትራቦካ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሜኖ ሲሞንስ፥ ማሻሻያው የሚጨበጥ ለውጥ እንደሚያመጣ እምነታቸው መሆኑን ገልፀው፥ መረጃዎቹን በመመልከት ምርጥ የቡና ምርቶችን አይነት ለመለየት ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቡና ምርቷ ብዝሃነት የአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ናት ያሉት ሜኖ ሲሞንስ፥ በጥራትም ኬንያ እና ኮሎምቢያን በማስከተል እንደምትመራ ገልፀዋል።

የባገርሽ ቡና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱላህ ባገርሽ፥ ማሻሻያው ህገወጥ የቡና ንግድን ለማዳከም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ገበሬዎች ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና እንዲያመርቱ ማበረታቻዎች የሚያገኙ በመሆኑም ጥራት ያለው ቡናን ለአለም ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

 

 

ምንጭ፦ https://www.ft.com/