በደብረ ማርቆስ በ684 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው የዘይት ፋብሪካ ከ70 በመቶ በላይ ተጠናቋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀን ከ135 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በቀጣይ አመት ወደ ምርት እንደሚገባ ተነግሯል።

ደብሊው ኤ በተባለ የዘይት ማምረቻና ማከፋፈያ ማህበር በደብረማርቆስ ከተማ፥ ኢንዱስትሪ መንደር እየተገነባ ያለው ፋብሪካ አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ግንባታ ተጠናቋል።

የማህበሩ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ እንግዳወርቅ መኮንን፥ ፋብሪካው ተጠናቆ ወደ ምርት ሲገባ ከውጪ በውድ ዋጋ እየተገዛ የሚገባውን የዘይት አቅርቦት ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል።

በ684 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ፋብሪካ በቀጣይ አመት መጨረሻ ላይ ወደ ማምረት ስራ ይገባል ተብሏል።

በአራት አይነት የቅባት እህሎች የዘይት ምርት ለማምረት ያቀደው ፋብሪካ፥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰሊጥ ዘይት ወደ ውጪ የመላክ እቅድም አለው።

በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምርም ለ650 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

 


በሃይለሚካኤል አበበ