ሳውዲ ስታር የሩዝ ልማቱን ወደ 10 ሺህ ሄክታር ለማስፋፋት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳውዲ ስታር የሩዝ ልማቱን ወደ 10 ሺህ ሄክታር ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማራው የሳውዲ ስታር የእርሻ ኩባንያ የአሌሮ ግድብን በመጠቀም ነው የመሰኖ ልማቱን ለማስፋት ያቀደው።

በኩባንያው የአበቦ እርሻ ልማት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አበራ እንደገለጹት፥ በዝናብ መቆራረጥ የሚታየውን የምርት መቀነስ ችግር ለማቃልል ኩባንያው የመስኖ ልማትን በስፋት ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰ ነው።

በአሁኑ ወቅትም የአሌሮ ግድብን በመጠቀም ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በመስኖ ሩዝ ለማልማት፥ የ32 ኪሎ ሜትር የውሃ መተላለፊያ ቦይ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው " ብለዋል ።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ በበኩሉ ኩባንያው የጀመረው ዘመናዊ የመስኖ ግብርና ልማት ለአካባቢው አርሶአደሮች ትልቅ ልምድና ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን ኢዜአ በዘገባው ጠቅሷል።