ለጥሬ እቃ የሚጣለው ቀረጥ ከአስመጪ ኩባንያዎች መብለጡ ተወዳዳሪነታቸውን እንደጎዳው እስክርቢቶ አምራቾች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገር ውስጥ ፋብሪካ አቁመን እስክሪብቶን ብናመርትም ለጥሬ እቃ የሚጣልብን ቀረጥ ያለቀለት እስክርቢቶን ከሚያስገቡ ኩባንያዎች መብለጡ ተወዳዳሪነታችን ላይ ችግር ፈጥሮብናል ሲሉ አምራች ፋብሪካዎች ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

ሶስት አምራቾች አሁን ላይ እስክርቢቶን በሀገር ውስጥ ለማምረት ፋብሪካን አቁመው በስራ ላይ ቢሆኑም፥ አምራቾቹ ተወዳዳሪነታችን ላይ ትልቅ ችግርን ያቆመ ነገር አለ ይላሉ።

እየተጣለብን ያለው ግብር አምራችነትን ሳይሆን ከውጭ አስገብቶ ማከፋፈልን የሚያበረታታ ሆኗልም ነው የሚሉት የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች።

እንደ እነርሱ ገለጻ ግብአትን ከውጭ ሀገር አስገብቶና ሰራተኛ ቀጥሮ ሀገር ውስጥ የሚያመርት ፋብሪካ፥ ያለቀ ምርቱን ከውጭ ከሚያስገባ አስመጪና አከፋፋይ ጋር እኩል ግብር ይከፍላል፤ አምራቹ የሚከፍለውም በልጦ ይታያል።

የፋንጉዙ ናኖ እስክርቢቶ ማምረቻ ፋብሪካ ሀላፊ አቶ ማሂር እስማኤል፥ ጥሬ እቃ ለማስገባት እየተጠየቁት ያለው ቀረጥ ችግር እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

በቀን 280 ሺህ እስክርቢቶዎችን በአራት አይነት ማምረት በሚያስችሉ ማሽኖች የተሞላው ይህ ፋብሪካ እስከ 200 ሰዎችንም መቅጠር ይችላል።

ሆኖም ሙሉ እስክርቢቶን ከሚያስመጡ ኩባንያዎች ጋር ግብር እኩል ሲያልፍም የሚበልጥ ገንዘብን መክፈላቸው ኪሳራ ውስጥ እንደጨመራቸው ነው የሚናገሩት።

በዘርፉ ላይ የተወዳዳሪነት ችግር ሲነሳ፥ የኬሚካል እና የኮንስትራክሽ ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ጥናትን ሰርቶ ነበር።

ጥናቱ ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2015 ባሉት አመታት እስክርቢቶን ከውጭ ገዝታ ለማስገባት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ እንዳወጣች ያሳያል።

ኢንቲትዩቱ በጥናቱ ላይ በኢትዮጵያ ያሉ ሶስት ፋብሪካዎች የሀገሪቱን አመታዊ የእስክርቢቶ ፍላጎት ማሟሏት እንደሚችሉ አረጓግጧል፤ በሀገሪቱ ለሚገኙ ተማሪዎችና የቢሮ ሰራተኞች ፍጆታ 154 ሚሊየን እስክርቢቶ ሀገሪቱ በአመት ያስፈልጋታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን ቢጠቀሙ ደግሞ በአመት 174 ሚሊየን እስክርቢቶን ማምረት ይችላሉ ይላል ጥናቱ።

የኤል ኢቲ ቢዝነስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዶክተር ኤርምያስ ገመቹ እንደሚሉት ደግሞ፥ ለጥሬ እቃ እየተጠየቁ ያሉት ቀረጥ ተወዳዳሪነታቸውን ጎድቶታል።

እስክርቢቶ ጫፍ ላይ የምትሰካውን ኮፐር ጥሬ እቃ ከውጭ ለማስገባት ብቻ 58 በመቶ ቀረጥ እንክፍላለን፥ ስለዚህ አስመጪዎች ከእኛ በረከሰ ዋጋ ስለሚሸጡ በልጠውናልም ነው ያሉት።

አሁን ላይ አስመጪዎች አንድን እስክርቢቶ በአማካይ 85 ሳምንቲም ሲሸጡ አምራቾች ደግሞ 90 ሳንቲም ይሸጣሉ፤ ይህ ዋጋም አምራቾች ለአንዱ ምርት ያወጣነው ነው ብለዋል።

በዚህም የተነሳ ትርፋማ መሆን ስላልቻልን ሰራተኞች ቀንሰናልም ነው ያሉት።

የኬሚካል እና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ ላይ ባጠናው ጥናት እስክርቢቶ አስመጪዎችና የሀገር ውስጥ አምራቾች በዚህ የቀረጥ ስርዓት መታየታቸው ተገቢ አለመሆኑን ያስቀምጣል።

አንድ እስክርቢቶ ከውጭ ሲገባ ቫት፣ ሱር ቀረጥና ዊዝሆልዲንግ ግብርን ሳይጨምር 30 በመቶ ሲቀረጥ፥ አምራቾች የሚያስመጡት ጥሬ እቃ ግን እያንዳንዱ ጥሬ እቃ እስከ 58 በመቶ ቀረጥ ይጣልበታል።

ይህን ለመቅረፍም አምራቾቹ ጥሬ እቃቸውን በዝቅተኛ ቀረጥ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ፥ ለገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሀሳብ ቀርቧል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ጉዳዩ በታሪፍ ኮሚቴ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

 

በካሳዬ ወልዴ