ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከችው የስጋ ምርት 72 ሚሊየን ዶላር ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የስጋ እና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከላከችው የስጋ ምርት 72 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷን አስታውቋል፡፡

ገቢው የተገኘው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ከተላከ የስጋ ምርት ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ካሊፋ ሁሴን እንደተናገሩት፥ ሳዑዲ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያን የበግ እና የፍየል ስጋ ምርት የሚገዙ ዋነኛ ሀገራት ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ካሊፋ ወደ ውጭ ከሚላከው ስጋ ምርት ውስጥ 60 በመቶው መዳረሻውን ወደ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ሲያደርግ፥ 38 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ሳዑዲ ትገዛለች ነው ያሉት፡፡

ቀሪው ሁለት በመቶ ወደ ውጭ የሚላከው የስጋ ምርትም ወደ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እንደሚላክ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ሁለቱ ሀገራት በየቀኑ 50 ቶን የስጋ ምርት እንደምትልክም አንስተዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

በኢትዮጵያ ስጋ አምራች እና ላኪዎች ማህበር ዋና ፀሃፊው አቶ አበባው መኮንን በበኩላቸው፥ ደረጃውን የጠበቀ የስጋ ምርት ለውጭ ንግድ ለማቅረብ ዘመናዊ የቤተ ሙከራ፣ የማቀዝቀዣ ስፍራ፣ የጭነት እና የማጓጓዣ አገልግሎቶች መመቻቸታቸውን ገልፀዋል፡፡

ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ የስጋ ምርት የሚያቀርቡ ደረጃቸውን የጠበቁ ቄራዎች መኖራቸውን ነው አቶ አበባው የጠቆሙት፡፡

ወደ ውጭ የሚላከው የስጋ ምርት ቀጣይነት እንዲኖረው ጥራት ያላቸውን የስጋ እንስሳት እንዲያቀርቡ ለከብት አድላቢ እና አርቢ ማህበራት በባለሙያዎች የታገዙ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ወደ ውጭ ከሚላክ የስጋ ምርት ከ150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዳለች፡፡

 

 

 

 

 

 

 


ምንጭ፡-ኢትዮጵያን ሄራልድ