በባህላዊ የወርቅ ምርት ስራ ውስጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ተስፋፍቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህላዊ የወርቅ ምርት ስራ ውስጥ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ስጋት እንደፈጠረበት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ገልጿል።

ባለፉት ስምንት ወራት ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ከሚገባቸው 6 ሺህ 638 ኪሎ ግራም ወርቅ ውስጥ 1 ሺህ 517 ኪሎ ግራም ብቻ ነው ያቀረቡት።

ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ከእቅዱ 30 በመቶ ሲሆን፥ ቀሪው በኮንትሮባንድ ሳቢያ ከሃገር የወጣ እና ለሃገር ገበያ በህገ ወጥ መንገድ የቀረበ መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።

ይህም የኮንትሮባንድ ንግድ በአሳሳቢ ደረጃ ለመስፋፋቱ ማሳያ መሆኑን ነው በሚኒስቴሩ የገበያ ልማት ትስስርና ትንበያ ዳይሬክተር አቶ ተወልደብርሃን አባይ ለኢዜአ የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥ ንግድ የተሰማሩ አካላት ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ግብይት በመፈፀም፥ የውጭ ምንዛሪ ማግኛና ሃብትን ወደ ውጭ የማሸሽያ መንገድ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ብለዋል።