የአገሪቷን ቱሪዝም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ተግባር በቀጣይ ወራት ይከናወናል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአገሪቷን ቱሪዝም አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መመደቡን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም አቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች የማስተዋወቁ ስራ በቀሪው ሩብ ዓመት እንደሚከናወንም ገልጿል።

የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትም ቱሪዝሙን በማስተዋወቅ የአገሪቷን መልካም ገጽታ ለመገንባት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጀቱ ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ባላቸው መገናኛ ብዙሃን የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል።

አዲሱን የቱሪዝም መለያ የአማርኛ አቻ ትርጓሜ "ምድረ-ቀደምት" ደግሞ ለአገር ውስጥ ቱሪስቶች እናስተዋውቃለን" ብለዋል።

አዲሱን የቱሪዝም መለያ 'ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ' በተለያዩ ቁሳቁሶችና የስጦታ እቃዎች ላይ በማተም ለማስተዋወቅ ሶስት ሚሊዮን ብር መበጀቱንም ገልጸዋል።

የአማርኛ አቻ ትርጓሜውን ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ለማስተዋወቅና ህዝቡም ይገልፀኛል ብሎ እንዲይዘው ለማድረግም ታቅዷል።

የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ እንደገለጹት፤ የቱሪስት ፍሰቱና ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ እስካሁን በመጣበት ሂደት ሳይሆን አመርቂ ውጤት እንዲመጣ ያስፈልጋል ።

በመሆኑም አዲሱን መለያ መሠረት በማድረግ የማኀበሩ አባላት አገሪቷን ለማስተዋወቅና ስነ ምግባርን ጠብቀው ለመስራት የበለጠ መነሳሳት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዜናዊ መስፍን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቱሪስቱ የሚመጥኑ ሆቴሎች እየተስፋፉ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህን በማስተዋወቅ ሂደት ማህበሩ "የሆቴል ጋይድ" አዘጋጅቶ በተለያዩ አገሮች እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

አዲሱ የቱሪዝም መለያ አገሪቷን በሚገባ እንደሚገልጻት የተናገሩት አቶ ዜናዊ፤ ይህን መለያ ስያሜ ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅና ገጽታዋን በመቀየር በኩል "የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል።

በተጨማሪም በፈጣን እድገት ላይ ያለው የሆቴል ቱሪዝም በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲቀናጅ በአገር ውስጥ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ከውጭ ባለሙያዎችን በማስመጣት ስልጠናዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ