በክልሎችና በከተሞች የተቀናጀ የንግድ መረጃ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የመረጃ ማዕከል እንደሚቋቋም ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)የተቀናጀ የንግድ መረጃ ስርዓት በአራት ክልሎችና ሁለት ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ የመረጃ ማዕከል እንደሚቋቋም የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ አለማር እንደተናገሩት ፥ የተቀናጀ የንግድ የመረጃ ስርዓት በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተሞች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ይደረጋል።

ለተግባራዊነቱም ከከተሞች አስተዳደርና ከክልሎች እንዲሁም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ከሚያደርገው የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ ጋር ስምምነት መደረሱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥የንግድ መረጃ ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገባ ለሸማቹ መረጃዎችን ያለምንም ግዜ ማባከን ባለበት ቦታ ሆኖ የት እንደሚያገኝና የሸቀጥ አይነትና ዋጋውን በቀላሉ እንዲያውቅ የሚያስችሉ ነው ብለዋል፡፡

ሸማቹ ሕብረተሰብ ከየክልሉ የሚመጡ ወቅታዊ መረጃ የሚያገኝበት አንድ ማዕከል የሚቋቋም ሲሆን፥የተቀናጀ የንግድ መረጃ ስርዓት ሸማቹ ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራት እና አይነት በቂ እና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ባለሥልጣኑ እነዚህ የንግድ የመረጃ ማዕከላት በመጪው ዓመት መስከረም እና ጥቅምት 2010 ዓ.ም ስራ እንደሚጀምሩ ገልጿል።

የመረጃ መሰብሰቢያ ማዕከላትም በየክልሎቹ እንደሚቋቋሙና ፋኩሊቲው በአሁኑ ወቅት የኮምፒውተር ሶፍትዌር የማበልጸግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቀሷል።

የሸማቹን መብት ለማስከበርና ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ለማስቻል ከተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ጉባኤ ጋር እየሰራ ይገኛል ነው የተባለው።

የመረጃ ማዕከሉ በባለሥልጣኑ የገበያ የመረጃ ዳይሬክቶሬት ስር እንደሚታዳደር እና የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን ዋጋ ከየአካባቢው በመሰብሰብ እና በማቀናጀት ለሸማቹ ህብረተሰብ የማሰራጨት ተልዕኮ እንዳለው ኢዜአ ዘግቧል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት አራቱን ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ከዋናው የገበያ መረጃ ማዕከል ጋር በማስተሳሰር፣ የንግድ ስራውን ለማዘመን፣ ከክልሎች ጋር ቀልጣፋ የንግድ መረጃ ልውውጥ ለመፍጠር እና አቅርቦትና ፍላጎትን የማጣጣም ስራ እንደሚያከናውን ገልጿል።

የአማራ ክልል ቀደም ብሎ የገበያ መረጃ ማዕከሉን በራሱ በማቋቋም ስራ መጀመሩ እንዲሁም በጋምቤላና በሶማሌ ክልሎች የገበያ መረጃ ማዕከላትን ለማቋቋም የሚያስችል ስራ ተጀምሯል፡፡

ባለሥልጣኑ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት ስድስት ክልሎች የገበያ መረጃ ማዕከላትን ለማቋቋም የሚያስችል መዋቅር በመዘርጋታቸው በየደረጃው ስራው እንደተጀመረ እና የተጀመረው በቀጣይም በሌሎች ክልሎች መዋቅሮች እንዲዘረጉና የንግድ መረጃ ማዕከላት እንዲፈጠሩ የማስቻል ስራ ይከናወናል።

ከዚህ በተጨማሪም እጥረት ባለበት አካባቢ አቅርቦትና ፍላጎትን ከማጣጣም አንፃር ነጋዴውም የአቅርቦት እጥረት ያለበትን አካባቢ እንዲያውቅ በማስቻል በኩልም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡