አጋጥሞ የነበረው የቤንዚን እጥረት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይፈታል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ አጋጥሞ የነበረው የቤንዚን እጥረት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እንደሚፈታ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ።

የድርጅቱ ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሃይለማርያም ለፋና ብሮድካስድቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ችግሩ ያጋጠመው ባህርዳር አካባቢ የሚገኝ ድልድይ ለጥገና ተብሎ ዝግ በመደረጉ ከሱዳን የሚመጣው የቤንዚን አቅርቦት ለጊዜው በመጓተቱ ነው።

ድርጅቱ ችግሩን ለመፍታትም መኪናዎቹ በወልድያ በኩል እንዲገቡ እያደረገ ሲሆን፥ ከጅቡቲ የሚገባውን የቤንዚን መጠን ከ11 መኪና ወደ 17 ከፍ አንዲል አድርጓል።

ሆኖም አሁን ላይ መኪናዎቹ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፥ ቤንዚኑ ኢታኖል እየተቀላቀለበት ወደ ማደያዎቹ ከሰዓታት በኋላ ይደርሳል ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

ኢትዮጵያ 40 በመቶ የቤንዚን አቅርቦቷን ከሱዳን ስትሸፍን ቀሪው በጅቡቲ በኩል የሚገባ ነው፤ በአጠቃላይ በቀን እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር ቤንዚን ትጠቀማለች።