ኢትዮ ቴሌ ኮም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮ ቴሌ ኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 15 ነጥብ 64 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ።

ኩባንያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ከገቢው ውስጥ 11 ነጥብ 91 ቢሊየን ብሩ ያልተጣራ ትርፍ ነው ብሏል።

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው ያለው።

በ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የደንበኞቹ ቁጥር ከ52 ሚሊየን በላይ መድረሱን ጠቁሟል።

ከዚህ ውስጥ 51 ሚሊየኑ የሞባይል ደንበኞች መሆናቸውን ነው የገለፀው።

የአገልግሎት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር ኩባንያው ሀገሪቱን በ13 ሰርክል በመከፋፈል ግዙፍ የቴሌ ኮም ማስፋፊያዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፥ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግሯል ።

በአጠቃላይም በመንፈቅ ዓመቱ ኩባንያው ያጋጠሙትን የሀይል መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማጭበርበርና መሰል ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልጿል ።