በመጋቢት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመጋቢት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ባለፉት አራት ወራት በነዳጅ ምርቶች ላይ በዓለም ገበያ ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ አሁን በስራ ላይ ያለውን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በመከለስ አዲስ ዋጋ አዘጋጅቷል።

በዚህም መሰረት በየካቲት ወር ላይ የነበረውን የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን በመከለስ ከመጋቢት 01 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ዋጋ ይፋ አድርጓል፡፡

በዋጋ ክለሳው መሰረት በአዲስ አበባ፥ ቤንዚን በሊትር 18 ብር ከ77 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍታ በሊትር 16 ብር ከ35 ሳንቲም፣ ነጭ ጋዝ በሊትር 16 ብር ከ35 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍታ በሊትር 14 ብር ከ01 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍታ በሊትር 13 ብር ከ37 ሳንቲም እንዲሆኑ ተወስኗል።

የአውሮፕላን ነዳጅም በሊትር 16 ብር ከ07 ሳንቲም በሆነ ዋጋ ይሸጣል።

የተደረገውን ማስተካከያ በሚመለከትም ሚኒስቴሩ የህዝብ ማስታወቂያ ያዘጋጀ ሲሆን፥ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ዝርዝር በነገው እለት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታትሞ ይወጣል።

ጭማሪው ከነገ መጋት 01 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።