የኢትዮ ቻይና የስሚንቶ ፎረም እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አመታዊ የስሚንቶ ምርት አቅማን 13 ሚሊዮን ቶን ያደረሰችው ኢትዮጵያ የውስጥ ፍላጎቷን አሟልታ ምርቱን ለውጪ ገበያም እያቀረበች ትገኛለች።

የኢትዮ ቻይና ስሚንቶ ፎረም የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የሀገሪቱ አመታዊ የስሚንቶ ፍላጎት በየአመቱ በ10 በመቶ እድገት እያሳየ መምጣቱ ተጠቁሟል።

በሀገር ውስጥ የሲሚንቶ ምርታማነት መጨመር የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት በመላክ ተጠቃሚ እያደረገ ነው ተብሏል።

ከዚህም ባሻገር በሀገር ውስጥ የሲሚንቶ ዋጋ እንዲረጋጋ ምክንያት መሆኑ ነው የተጠቀሰው።

የሲሚንቶ ምርታማነቱ ማደጉ ቤት እና ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን ለሚገነቡት መንግስት እና ህዝብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አለሙ ስሜ ተናግረዋል።

የስሚንቶ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈጣን እድገት ቢታይበትም የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ፈተናው አሁንም አልተቀረፈም።

በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ችግር ለመቅረፍ ኢንዱስትሪውን የሚመራ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን የሚያፋጥን፣ እንዲሁም ጥናት እና ምርምር የሚያደርግ የሰው ሀይል ለመፍጠር መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

የሰው ሀይል ክፍተቱን ለመድፈን የስሚንቶ ቴክኖሎጂ ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

በአዲስ አበባ እና አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የልህቀት እና የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ማዕከል ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተጠቅሷል።

አዲስ በተቋቋመው የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩትም የማቴሪያል ሳይንስ ዳይሬክቶሬት የቴክኖሎጂ ክፍል ተቋቁሞ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀብት ለማፍራት ጥረት እየተደረገ ነው።

እነዚህ ስራዎችም በአጠቃላይ በሲሚንቶ ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ያግዛሉ ተብሏል።


የኢትዮ ቻይና ስሚንቶ ፎረም ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ይቀጥላል።


በደመቀ ጌታቸው