የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምርቱን ለውጭ ገበያ ላከ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረተ የመጀመሪያ ምርት ለውጭ ገበያ ተላከ።

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅ ምርት የተሠማራው ኤፒክ የተባለ ድርጅት ነው ምርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት ለውጭ ሃገር ገበያ የላከው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ፥ ኤፒክ ምርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ ማቅረቡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዘርፍ የተመዘገበ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም በዘርፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንዲሁም መንግሥት የሚያደርገው ድጎማ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል።

"በሚቀጥለው ሳምንትም ሸሚዝ አምራቹ ታል ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያን ጨምሮ ሌሎችም ድርጅቶች እግር በእግር ምርታቸውን ወደ አሜሪካ፣ ካናዳና ኖሮዌይ ይልካሉ" ብለዋል።

መቀመጫውን ሆንግኮንግ ያደረገው የኤፒክ ድርጅት ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ቻንዳና ሎኩግ፥ ምርታቸውን ኤክስፖርት በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የህፃናት አልባሳት የሚያመርተው ኩባንያቸው ፓርኩ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮችን በአንድ ላይ በመያዙ ለስራቸው ተስማሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአጎዋ ስምምነትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የቀረጥና ግብር እፎይታ መስጠቱ ከሌሎች ሃገራት አንጻር በዝቅተኛ ዋጋ የሰው ሃይል መገኘቱና የመብራት ክፍያ ዝቅተኛ መሆኑ በሃገሪቱ ለመስራት ምቹ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል።

በመጀመሪያው ዙር 40 ሺህ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት አሜሪካን አገር እንደሚልኩ የተናገሩት ቻንዳና፥ እለቱ ህልማቸው እውን የሆነበት ቀን መሆኑን በመግለጽ በመንግሥትም ሆነ በፓርኩ ሠራተኞች ለሚደረግላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ባለፈው ዓመት ተመርቆ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፥ ከ60 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎችም የስራ እድል የመፍጠር አቅም ያለው ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ

android_ads__.jpg