ቤላሩስ ከኢራን ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ማጓጓዣ መርከብ ገዛች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤላሩሱ ቤል ነዳጅ ዘይት ድርጅት 6 መቶ ሺህ በርሜል ቀላልና ከባድ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ማጓጓዝ አቅም ያለው መርከብ ከኢራን ብሄራዊ ነዳጅ ዘይት ኩባንያ ገዛ፡፡

ቤል ነዳጅ ዘይት ድርጅት የጭነት መርከቡን የሚጠቀምበት ከኢራን ለሚገዛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ሲሆን ፥ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ጭነቱን ወደ ጥቁር ባህር ኦዴሳ ወደብ ወይም የባልቲክ ወደብ የሆነችው ቬንትሰፒልስ ለማጓጓዝ ይጠቀምበታል ተብሏል፡፡

ጭነት መርከቡ በዚህ ወር መጨረሻ ግድም ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከኢራን በመግዛት ከካሃርግ ደሴት ይጭናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሩሲያ ካለፈው አመት ጀምሮ በዋጋ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለቤላሩስ የምትሸጠውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት አቅርቦት ማቋረጧን ተከትሎ ቤላሩስ ሌሎች አማራጮችን እየፈለገች ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ሩሲያ ለቤላሩስ ልትሸጥ ካቀደችው 24 ሚሊዮን ቶን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ውስጥ በመቀነስ 18 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው የሸጠችላት፡፡

ባለፈው አመት በነሃሴ ወር ፖላንድ በተመሳሳይ መልኩ የነዳጅ ዘይት ግዢዋን ከሩሲያ ወደ ኢራን አዛውራለች፡፡

ሁለት ሚሊዮን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በርሜሎች ከኢራን ወደ ፖላንድ እየተጓጓዘ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ይህ የፖላድ እርምጃ በነዳጅ ዘይት አቅርቦት ዙሪያ በሩሲያ ላይ ያለውን መተማመን ለመቀነስ ማሰቧን ያመለክታል ተብሏል፡፡

የፖሊሲ አማካሪዎች እንደሚሉት ሩሲያ ከምዕራባውያን ጋር በገባችው ውዝግብ መነሻ የሃይል ዋስትና ስጋት ላይ እየወደቀ ነው፡፡

ምንጭ ፦ ፕሬስ ቲቪ

ተተርጉሞ የተጫነው፦በእስክንድር ከበደ